ክልሉ በቀጣይ የኑሮ ዉድነትን ለማረጋጋት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል – የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ

ሀዋሳ፡ ጥር 29/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ክልሉ በቀጣይ የኑሮ ዉድነትን ለማረጋጋት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊና የንግድ ስርዓትና ሸማች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ይስሀቅ ማሶሬ አስታዉቀዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የኑሮ ዉድነትን ለማረጋጋት በሚያስችሉ ተግባራት ላይና

የ2016 ዓ.ም የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ ጋር በቡታጂራ ከተማ አካሂዷል።

ባለፋት 6 ወራት አምራችና ሸማቾችን በቀጥታ እንዲገናኙ የማድረግ ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል።

የኑሮ ውድነትን በሚያባብሱ ህገ-ወጥ አካላት ላይ እርምጃ በመውሰድና ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ ባለፋት 6 ወራት የተሰሩ ስራዎች በቀጣይ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

የንግዱን ማህበረሰብ ከሸማቹ ጋር በማስተሳሰር በሚሰሩ ስራዎች ዉጤት ማስመዝገብ መቻሉንና ቢሮው አዲስ እንደመሆኑ የሰው ኃይልና አስፈላጊ እቃዎችን የማሟላት ስራ ጎን ለጎን በግማሽ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ዉጤት መመዝገቡን ነው ምክትል ኃላፊዉ የገለፁት።

ምክትል ቢሮ ኃላፊና የገበያ ግብይት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ቀመርያ ረሺድ በበኩላቸዉ የነዳጅ ግብይትን በተመለከተ በቀጣይ በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም በትኩረት የሚሰራበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የኑሮ ዉድነት የሚያባብሱ ነጋዴዎችንና ህገወጥ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የስልጤ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸምሱ ኑሪ እና የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ብርሃኔ በጋራ እንደገለፁት፤ የኑሮ ዉድነትን ለማረጋጋት የጋራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን በመጥቀስ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠር አምራች አርሶ አደሩን ከሸማች ጋር በማገናኘት ጠንካራ የመፍትሔ እርምጃዎች እየተሰሩ ነዉ።

በንግድ ስርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ስርዓቱን ማዘመን ፍትሃዊ በማድረግ ረገድ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሰንበት ገበያ ላይ በቂ ምርት ለማቅረብ እየተደረገ ባለዉ ጥረትም ከማህበረሰቡና ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ትስስር በማድረግ የሚታዩ የምርት እጥረቶችን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰሩ ይገልፀዋል።

አክለውም ከመድረኩ ባገኙት ግንዛቤ መሠረት በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በመድረኩ የኮንትሮባንድ ንግድን ተከታትሎ እርምጃ አለመዉሰድ፣ የህገወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነት፣ የግብይት ስርዓትን በቴክኖሎጂ የማዘመን ዉስንነት፣ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ውስንነትና ሌሎች ጥያቄዎች ከባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች ተነስተዋል።

ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት በቀጠይ በሚሰሩ ስራዎች ዙሪያ አቅጣጫ ተቀምጧል።

በመድረኩ ለመወያያ በቀረቡ አዋጅና መመሪያ ሠነዶች ላይ ውይይት በማድረግ በክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠዉ ማጠቃለያ ተደርጎበታል።

ዘጋቢ፡ ብዙነሽ ዘውዱ