ሀዋሳ፡ ጥር 29/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጉራጌ ዞን አስተዳደር እና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የዘቢዳር አትሌቲክስ ክለብን ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ሠነድ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማና የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል ፈርመዋል።
ከተመሠረተ ከ10 አመታት በላይ ያስቆጠረው እና በጉራጌ ዞን የሚገኘው ዘቢዳር አትሌቲክስ ክለብ ያስቆጠረውን አመት ያህል ውጤታማ ሳይሆን ቆይቷል።
ክለቡ በሚፈለገው ደረጃ እንዲያድግ ድጋፍ የሚያስፈልገው በመሆኑ የጉራጌ ዞን አስተዳደር ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር ክለቡን ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል በስምምነቱ ወቅት እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት አንዱ የተቋቋመለት አላማ በመሆኑ ለአትሌቲክስ ክለቡ የምሁራን ሙያዊ ስልጠናን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል።
ማዕከሉ ዕውቅ አትሌቶች የሚወጡበት ሆኖ ማየት እንመኛለን ያሉት ፕሬዝዳንቱ ለዚህም ዩኒቨርሲቲው በሚችለው ሁሉ አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው አትሌቲክስ ክለቡን ለማጠናከር በርካታ ስራዎች መሠራት እንዳለባቸው ጠቁመው ይህ ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተደረገው የድጋፍ ስምምነትም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።
ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በስፖርቱ ዘርፍ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ለስፖርቱ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን በማሟላት የዘቢዳር አትሌቲክስ ክለብን ለመደገፍ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ገልፀዋል።
የዘቢደር አትሌቲክስ ክለብ ካሉበት ተደራራቢ ችግሮች ይላቀቅ ዘንድ ይህ ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተደረገው ስምምነት ቁልፍ ሚና ይጫወታል ያሉት ደግሞ የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሄኖክ አብዱልሠመድ ናቸው።
በተደረገው ስምምነት መሠረት ዩኒቨርሲቲው የሚያደርጋቸውን ድጋፎች በኃላፊነትና በፍትሀዊነት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራም ኃላፊው ገልፀዋል።
ከጉራጌ ዞን አስተዳደር፣ ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና ከዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት የመግባቢያ ስምምነቱ የፊርማ ስነ-ስርአት ተከናውኗል።
ዘጋቢ፡ አሰፋ ፀጋዬ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ