ሀገራዊ የልማት ለውጦች እንዲሳኩ ኃላፊነታችንን እንወጣለን ሲሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የፋይናንሰና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሰራተኞች ገለጹ

ሀዋሳ፡ ጥር 29/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተለያዩ ዘርፎች የተጀመሩ ሀገራዊ የልማት ለውጦች እንዲሳኩ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፋይናንሰና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሰራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡

ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የቆየው የሠራተኞች አቅም ግንባታ ሰልጠና ተጠናቋል፡፡

ሀገራዊ ለውጥን ተከትሎ እየተመዘገቡ ባሉት የልማት እምርታዎችና ያጋጠሙ ፈተናዎችንና ተግዳሮቶችን ወደ መልካም ዕድል ለመቀየር እየተከናወኑ ባሉት እንቅስቃሴዎች ላይ የመንግስት ሠራተኞች የጋራ ሀገራዊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያለመ መድረክ ለሁለት ቀናት ተካሂዷል፡፡

በስልጠና መድረኩ ላይ ከተሳተፉት ሠራተኞች መካከል አንዳንዶች በሰጡት አሰተያየት፥ ከተሰጣቸው የአቅም ግንባታ ስልጠና የተሻለ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ጠቁመው፥ በቀጣይ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት በመሰጠት የተጀመሩ ሀገራዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ለውጦች ስኬታማ እንዲሆኑ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል:.

የቢሮ ምክትልና የፋይናንስ ዘርፍ ሀላፊ አቶ መሰለ ኡሮ፥ ያሉንን ጸጋዎች በመለየት ሀብት ለመፍጠር ሲቪል ሰርቫንቱ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መሰል የአቅም ግንባታ ሰልጠናዎች ከፍተኛ አሰተዋጽኦ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

ከስልጠናው የተገኘውን ዕውቀት በመተግበር ሚናቸውን እንደሚወጡም አቶ መሰለ አክለዋል፡፡

በቢሮው የግዥና ንብረት አሰተዳደር ኤገንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ የሺሀረግ ደበበ በበኩላቸው፥ የመንግስት ሰራተኞች ሀገራዊ ፖሊሲዎችንና እስትራቲጂዎችን በመገንዘብ የተቋማቸው ተልዕኮ እንዲሳካ የአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ሀገራዊ ተልዕኮውን የሚሸከምና ለሀገረ መንግስት ግንባታ የድርሻውን መወጣት የሚችል ብቁ ዜጋን ማፍራት ደግሞ የሀገር ሐብት እንዲጨምር ፋይዳው ሰፊ ነው ያሉት የቢሮው ሀላፊ ወ/ሮ ወሰነች ቶማሰ ሲቪል ሰርቫንት ቀልጣፋና ጊዜውን በአግባቡ የሚወጣ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ብዙአየሁ ጫካ – ከቦንጋ ጣቢያችን