የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ይበልጥ ለማሳደግ የፐብሊክ ሰርቫንቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ጥር 29/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ይበልጥ ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብ የፐብሊክ ሰርቫንቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

በከተማው የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ጽ/ቤት የ2016 ዓ/ም አፈፃፀም መነሻ ለተቋማትና ፈጻሚዎች እውቅናና ሽልማት የመስጠት መርሃ ግብር ተካሂዷል።

መድረኩን የከፈቱት የይርጋጨፌ ከተማ ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን፥ እውቅናና የሽልማቱ የተሻለ የፈጸሙ ሠራተኞችን በማበረታታት በአፈፃፀም ወደ ኋላ የቀሩትን ለማነሳሳትና ለተሻለ ውጤት ለማዘጋጀት ታስቦ እንደሆነ አንስተዋል።

የከተማውን ዕድገት ለማረጋገጥና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ይበልጥ ለማሳደግ በሚደረገው ርብርብ የፐብሊክ ሰርቫንቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት አቶ ታደለ፥ የተሻለ ውጤት  ለማስመዝገብ ቅንጅታዊ ሥርዓት ተዘርግቶ መሠራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

የተቋማት ውጤት የሚለካው በከተማው በተመዘገበ ውጤትና በተገልጋዮች እርካታ መነሻ ሊሆን ይገባል ያሉት ከንቲባው፥ ሁሉም ሠራተኞች ተቋማዊ አሠራርን በጠበቀ መልኩ ተግባራትን በመፈፀም ለተሻለ ውጤት እንዲረባረቡ ጠይቀዋል፡፡

የከተማው ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ ዓለሙ በየተቋማቱ ከተመዘገቡ ውጤቶች የላቀ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ተቋማት ውጤት ተሞክሮ በመቀመር በሁሉም ሴክተር መስሪያቤቶች ወጥና ተቀራራቢ ውጤት እንዲመዘገብ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጉባኤው ተሳታፊ ሠራተኞች በበኩላቸው በሠራተኞች መካከል እኩል ያለመንቀሳቀስ ችግር መኖሩን በመጥቀስ የምዘናና የውጤት አሰጣጥ ሥርዓት መታየት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

በየሴክተሩ የሚስተዋሉ የሎጅስቲክ እጥረት እንዲቀረፍላቸው ያሳሰቡት ሠራተኞቹ በተለይም አሁን ላይ ካለው ከኑሮ ውድነት ሳቢያ የመንግሥት ሠራተኞች በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈተኑ መሆናቸውን በመጠቆም፥ መንግሥት የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ጉዳይ ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

በከተማው እየተከናወኑ ባሉ በልማትና በመልካም አስተዳደር ሥራ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ሠራተኞች የእውቅናና ሽልማት የመስጠት ሥነ ስርዓት ተከናውኗል፡፡

ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን