የታክስ ስወራና ማጭበርበርን ለመከላከል በቅንጅት ይሠራል- ቢሮው

የታክስ ስወራና ማጭበርበርን ለመከላከል በቅንጅት ይሠራል- ቢሮው

ሀዋሳ፡ ጥር 28/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የታክስ ስወራና ማጭበርበር ወንጀሎችን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ገለጸ፡፡

በክልሉ በሚፈፀሙ የታክስ ስወራና ማጭበርበር ወንጀሎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ በጎፋ ዞን ሣውላ ከተማ ተካሂዷል።

በምክክር መድረኩ የተገኙት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ ገቢ ለአንድ ሀገር እድገት ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን አንስተው የታክስ ስወራና ማጭበርበር ወንጀሎችን የሚፈጽሙ አካላትን ወደ ሕግ ከማቅረብ አኳያ የፍትህ ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዓለምነሽ ደመቀ በበኩላቸው ቢሮው ከህዝቡ ለሚነሱ የልማት ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በገቢ አሰባሰብ ሂደት የሚሰተዋለውን የታክስ ማጭበርበር ወንጀል ከህግ አካላትጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አመላክተዋል ፡፡

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ፋንታዬ ለሀገር ዕድገትና ልማት ጠንቅ የሆነውን የታክስ ስወራና ማጭበርበር ወንጀሎችን ለመከላከልና የመንግስትና የሕዝብን ሀብት ከምዝበራ ለመታደግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደ ሚቀጥሉ ተናግረዋል ፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች የኦዲት ግኝት ፣ ሀሰተኛ ደረሰኝ መበራከትና የገቢ አሰባሰብ ችግሮችን ለመፍታት በህግ አግባብ የሚሰሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አንሰተዋል፡፡

ዘጋቢ : ስንታየሁ ሙላቱ- ከሳውላ ጣቢያችን