የህዝብንና የመንግስትን ሀብት ለተገቢው አገልግሎት እንዲውል የኦዲት ሽፋኑን ማስፋት እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጥር 28/2016 ዓ.2016 (ደሬቴድ) የህዝብንና የመንግስትን ሀብት ለተገቢው አገልግሎት እንዲውል የኦዲት ሽፋኑን ማስፋት እንደሚገባ ተገልጿል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ፕላን መሠረተ ልማትና የመንግስት ሀብት አስተዳደር ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን ዋና ኦዲተር ቢሮን ገምግሟል።
የክልሉ ም/ቤት ፕላን መሠረተ ልማትና የመንግስት ሀብት አስተዳደር ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን ዋና ኦዲተር ቢሮ የ6 ወር አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት የክልሉ ዋና ኦዲተር ቢሮ ሀላፊ አቶ አበባየሁ ኤርምያስ የቢሮውን የ6 ወር እቅድ አፈጻጸም ሲያቀርቡ እንደገለጹት ለኦዲት ተደራጊ መ/ቤቶች ክትትልና ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።
የክዋኔ ኦዲት ጋር ተያይዞ ሶስት ተቋማት የኦዲት ክትትል ለማድረግ ታቅዶ በአግባቡ መከናወኑን ተናግረዋል።
እነዚህና መሰል ተግባራት መከናወናቸውን የተናገሩት አቶ አበባየሁ የሠው ሀይል እጥረትና የአይቤክስ ሲስተም መሠረተ ልማት አለመሟላት ለእቅድ አፈጻጸሙ እንቅፋት እንደነበረ አንስተዋል።
አፈጻጸሙን መነሻ በማድረግ ተቋማትን ወርዶ ከማየትና ከመገምገም አኳያ የተከናወነው ተግባር የተሻለ መሆኑን ከቋሚ ኮሚቴ አባላት አስተያየት ተሰጥቷል።
እንደዚሁም የኦዲት ስራው በተገቢው መንገድ እየሄደ ቢሆንም ምዝበራው በታችኛው ተቋማት ላይ በስፋት ስለሚታይ ትኩረት ቢደረግ ሲሉም አንስተዋል።
ኦዲት ጥራት ጋር ተያይዞ የመንግስት ሀብትና ንብረት ለታለመለት አላማ እንዲውል ከማድረግ አኳያ ውስንነቶች እንደሚስተዋሉ ከቋሚ ኮሚቴ አባላት ተነስቷል።
የዋና ኦዲተር ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ አባይነህ አቹላ በሰጡት ምላሽ የተቋማትን የውስጥ ኦዲት በማጠናከር የንብረትና የገንዘብ ሀብት አጠቃቀምን መከታተል ይገባል።
ከክዋኔ ኦዲት አንጻር በቀጣይ እቅዱን በማስፋት እንደሚሰሩና በመረጃ የተደገፉ የኦዲት ግኝቶችን በይበልጥ ትኩረት በማድረግ እንደሚሰራ አንስተዋል።
የቢሮው ዋና ሀላፊ አቶ አበባየሁ ኤርምያስ በበኩላቸው ተአማኒነት ያለውና ውጤት ያለው ስራ ከመስራት ባሻገር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እንደሚሰሩ አንስተዋል።
በቀጣይ ከንብረት ማስመለስ ጋር ተያይዞ ሰፊ ክትትል በፋይናንስ ረገድ መደረግ እንዳለበትና የውስጥ ኦዲት ባለሙያዎችን አቅም ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል አቶ አበባየሁ።
የፕላን መሠረተ ልማትና የመንግስት ሀብት አስተደደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እንቁ ዮሀንስ በበኩላቸው በተቋሙ የተጀመሩ ቀልጣፋ አሰራሮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና የክዋኔ ኦዲት ግኝት ማደግ እንዳለበት አንስተዋል።
እንደዚሁም የኦዲት ሽፋን ጉዳይ አፈጻጸሙ የተሻለ ቢሆንም ርምጃ የሚወሰድበት አግባብ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ