የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በቀጣይ ስድስት ወራት 7 ነጥብ 9 በመቶ ያድጋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

ሀዋሳ፡ ጥር 28/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በቀጣይ ስድስት ወራት 7 ነጥብ 9 በመቶ የሚያድግ መሆኑን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ እየሰጡ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በርካታ ተግዳሮቶችን በመሻገር አመረቂ ውጤት እየተመዘገበ ነው።

በአለም አቀፍ መመዘኛ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ 7 ነጥብ 9 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ብለዋል።

በሃገሪቱ ፊስካል ፖሊስ ዘርፍ ላይ በተወሰዱ እርምጃዎች በሃገሪቱ ዋና ዋና ምጣኔ ሃብቶች ላይ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውንም አረጋግጠዋል።

የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ከድጎማ ወጪ ነጻ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት በርካታ ድርጅቶች ከእዳ ነጻ ተደርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአብነት የነዳጅ አቅራቢ ድርጅትን ያነሱ ሲሆን ድርጅቱ እስከ 190 ቢሊዮን ብር እዳ የነበረበት ሲሆን አሁን ላይ ወደ 100 ቢሊዮን ብር ዝቅ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

በሌሎች ድርጅቶችና ተቋማት በተመሳሳይ መልኩ በተሰሩ ማስተካከያዎችም ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

አለም አቀፍ ችግር የሆነውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ ነውም ብለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ የፋይናንስ ተቋማት 170 ቢሊዮን ብር ብድር ማሰራጨታቸውን ያነሱት ዶክተር ዐቢይ 83 በመቶ የሚሆነው ለግሉ ዘርፍ መሰራጨቱ ትልቅ ስኬት መሆኑን አንስተዋል።

በገቢ ረገድ ባለፉት ስድስት ወራት 270 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ የተያዘ ሲሆን አሁን ላይ 265 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል። የእቅዱ 98 በመቶ ነው ብለዋል።

አዘጋጅ፡ ጀማል የሱፍ