የክትትልና ግምገማ ስርአትን በቅንጅት በመምራት የፍርድ ቤቶች ውጤታማነት ማረጋገጥ ይገባል – የጉራጌ ዞን ምክር ቤት

ሀዋሳ፡ ጥር 28/2016 ዓ.2016 (ደሬቴድ) የክትትልና ግምገማ ስርአትን በቅንጅት በመምራት የፍርድ ቤቶች ውጤታማነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አስታወቀ።

በዞኑ የሚገኙ የከተማና ወረዳ አስተዳደር አፈጉባኤዎችና የፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች በፍርድ ቤቶች የሪፎርም ፍኖተ ካርታ ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂደዋል።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወ/ሮ  ልክነሽ ስርገማ በዚህ ወቅት እንዳሉት ማንኛውም ሰው በህግ ፊት ያለማንም ጣልቃገብነት በፍርድ ቤቶች ውሳኔ ማግኘት እንደሚችል ማረጋገጥ ይገባል።

ጥራት ያለውና ተአማኒቱን ያተረፈ የዳኝነት ስርአት ለማስፈን ተገቢውን  መረጃ ተደራሽ ማድረግ የፍኖተ ካርታው አንዱ አላማ መሆኑን ገልጸው የፍትህ መዘግየት እና መጓተት በማህበረሰቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ለዘርፉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት መስጠት እደሚገባ ተናግረዋል።

የፍርድ ቤቶች የሪፎርም ፍኖተ ካርታ እስከ ታችኛው መዋቅር በወቅቱ ተደራሽ ማድረግ አሰፈላጊ መሆኑን በማመላከት በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የፍትህ ስርአት ለመዘርጋት የክትትልና  ግምገማ ስርአቱ በቅንጅት በመምራት የፍርድ ቤቶች ውጤታማነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ወ/ሮ ልክነሽ አሳበዋል።

በመድረኩ የፍርድ ቤቶች ፍኖተ ካርታ በተመለከተ ሰነድ የቀረበ ሲሆን ተቀባይነትና ጥራት ያለው እንዲሁም የዳኝነት አስተዳደር ውጤታማ ለማድረግ ግብ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱን ተገልጿል።

ግልፀኝነትና ተአማኒነት ያለው እንዲሁም  የፍርድ ስርአቱ ቀልጣፋ ለማድረግ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መታገዝ እንዳለበት በመጠቆም ዳኞች የህዝብ አገልጋይነት ስሜት እንዲኖራቸው መስራት ሌላኛው የትኩረት መስክ መሆኑም ተመላክቷል።

ከተሳታፊዎች መካከል የጉንችሬ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ምትኩ ደንቢ፣ የወልቂጤ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ወጉ እና የእንደጋኝ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ገረመች ዘርፉ ይገኙበታል።

በሰጡት አስተያየትም የዳኞች አመለካከት፣ እውቀት እና ተደራሽነት ላይ መሰራት እንዳለበት አንስተዋል።

አንዳንድ አዋጆች ጊዜው በሚመጥን መልኩ ባለመሻሻላቸው ውሳኔ ላይ ክፍተት መፍጠሩን ተናግረው በተጨማሪም ጥቅማጥቅም እና ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠር በኩል ትኩረት ባለመሰጠቱ የህግ የበላይነት ለማስከበር እንቅፋት መሆኑንም ገልፀዋል።

ከፍርድ ቤቶችና ፍትህ ተቋማት እውቅና ውጪ በሀገር ሽማግሌዎችና ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች የሚሰጥ ብይን ብዙዎችን ከማህበራዊ ህይወት እያፈናቀለ በመሆኑ ዘርፉ ክትትልና ድጋፍ እደሚያስፈልገውም አመላክተዋል።

የጉራጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሞሲሳ ቆርቻ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እደተናገሩት  ህዝቡ በፍትህ እጦት እና በመልካም አስተዳደር እንዳይሰቃይ በቅንጅት  መስራት አስፈላጊ በመሆኑ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል።

አሁን ላይ ጊዜውን የዋጀ አዋጅ ወጥቶ ለመተግበር ወደ ተግባር መገባቱንና የዳኞች ጥቅማጥቅም ለማስከበርም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ሞሲሳ አመላክተዋል።

በፍርድ ቤቶች ጣልቃ ገብነት ከግለሰብ እስከ መንግስት ተቋም ድረስ በመኖሩ ዘርፉን ፈታኝ እያደረገው መሆኑን ጠቅሰው ይሁን እንጂ ዳኞች ያለማንም ጣልቃገብነት ነፃ ሆነው ተግባራቸውን አዲፈፅሙ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በወልቂጤ ከተማ በጉብሬ ክፍለ ከተማ ተቋርጦ የነበረው የመሬት ክርክር   ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑንም  ገልጸዋል።

በአንዳንድ ቦታዎች ከህግ የበላይነት ካለማክበር ጋር ተያይዞ ምስክሮች በነፃነት ቃላቸውን ለመስጠት እንደሚቸገሩ በማንሳት በቀጣይ ችግሩን መቅረፍ እንዲቻልም ትኩረት ተሠጥቶ እየተሰራ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

ዳኛ የሌላቸው መዋቅሮችን በመለየት ለማሟላት እየተሰራ ነው ብለዋል አቶ ሞሲሳ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ።

በንቅናቄ መድረኩ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የወረዳና ከተማ አስተዳደር አፈጉባኤዎች እና የፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ እንዳልካቸው ደሳለኝ – ከወልቂጤ ጣቢያችን