ሀዋሳ፡ ጥር 26/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የተቀናጀ ተፋሰስ እና የበጋ ልማት ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ በተለይም አመራሩ አርሶ አደሩን በማቀናጀት መስራት እንዳለበት የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን ገለፁ።
የዞኑ ግብርና መምሪያ በተቀናጀ ተፋሰስ ልማትና ወቅታዊ የግብርና ስራዎች ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ በቡኢ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን ዞኑ በተቀናጀ የመስኖ ስራ አቅም ያለው መሆኑን ጠቅሰው የዘንድሮው የተፋሰስና የበጋ ልማት ስራዎችን አጠናክሮ በማሰቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ለዚህም ውጤታማነት በየደረጃው በሚደረገው ጥረትም በተለይም አመራሩ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት አርሶ አደሩን በማቀናጀት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ደሱ አበጋዝ ባቀረቡት ሰነድ ላይ በ2016 በአፈርና ውሀ ጥበቃ ሥራ 93 ነባርና ንዑስ ተፋሰሶችን 15 ሺህ 542 ሄክታር መሬት እንደሚለማ ተናግረዋል።
ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ከ21 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ ጠቅሰው በዚህም 21 የቤተሰብና የማህበረሰብ አቀፍ የገንዳ ቁፍሮ እንደሚካሄድም ገልፀዋል።
የአፈር ጤንነትና ለምነትን ለማሻሻል በአሲዳማነት የተጠቃ 426 ሄክታር መሬት በማከም 9 ሺህ 630 ኩንታል ኖራ ለማቅረብ መታቀዱን አስረድተዋል።
በተፋሰስ ልማቱ 146 ሺህ 141 የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ የጠቆሙት አቶ ደሱ በለሙ ተፋሰሶች ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር በመኖ ልማት፣ በንብ ማነብ፣ በፍራፍሬና በአትክልት ስራዎች እንዲሳተፉ እንደሚሰራም አብራርተዋል።
በ2016 በበልግ እርሻ 392 ሺህ 907 ሄክታር መሬት በተለያዩ የአዝርዕት ሰብል እንደሚለማ ጠቅሰው ከዚህም 49 ሚሊዮን 915 ሺህ 208 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።
በአትክልት ልማት 103 ሺህ 324 ሄክታር መሬት በማልማት 22 ሚሊዮን 941 ሺህ 781 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።
የበጋ አረንጓዴ ችግኝ ተከላ ከ24 ሚሊየን በላይ ችግኝ እንደሚተከል አብራርተው የመኖ እጥረትን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራም ሀላፊው ገልጸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የተሰሩ የተፋሰስ ሰራዎች እንዳይበላሹ በማድረግ የለሙትን ለወጣቱ በማስረከብ የስራ እድል መፍጠር እንደሚገባ ገልፀው በተለይም ምርጥ ዘር ላይ ያለውን እጥረት ላይ መስራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
የተቀናጀ ተፋሰስና የበጋ ግብርና ስራዎችን ለማሳካት በቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በዞኑ የዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የማስጀመሪያ መርሃግብር ጥር 30/2016 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ተግባሩም ለ30 ቀናት እንደሚቆይ ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ፡ ትግሥት ተሾመ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ