ሀዋሳ፡ ጥር 26/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለክልሉ ህዝብ የተሻለና የዘመነ የጤና አገለግሎት ተደራሽ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አልማው ዘውዴ ገለጹ፡፡
ላለፉት ሁለት ቀናት በታርጫ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የ2016 ዓ.ም የግማሽ አመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ጉባኤ ተጠናቋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አልማው ዘውዴ ለክልሉ ህዝብ የተሻለና የዘመነ የጤና አገለግሎት ተደራሽ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው በክልሉ ባለፉት ሰድስት ወራት በጤና ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ክፍተቶችን ለማረም በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተገልፀዋል።
የጤና ኤክስቴንሽን ፍኖተ ካርታ ለማጠናከር የፖለቲካ አመራርና የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ክትትልን ጨምሮ በጀት መመደብ፣ ፍኖተ ካርታውን ማስተዋወቅ እንዲሁም የህብረተሰብ ተሳትፎና ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ላይ ልዩ ትኩረት ይሰጣልም ብለዋል።
ከፍተኛ የወባ በሽታ ስርጭት፣ ኩፍኝና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የክልሉ የማህበረሰብ ጤና ተግዳሮት መሆኑ በሰፊው የተነሳ ሲሆን እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ሁሉ አቀፍ ርብርብና ድጋፍ ያስፈልጋል ተብሏል።
ባለፉት ስድስት ወራት 1 ነጥብ 2 ሚልዮን የአልጋ አጎበር ማሰራጨትን ጨምሮ በርካታ የወባ መከላከል ስራ ቢሰራም ህብረተሰቡ የወባ መከላከያ መንገዶችን በሚገባ ተግባራዊ ካለማድረግ የተነሳ የወባ በሽታ ስርጭት በክልሉ ከፍተኛ መሆኑም ተጠቁሟል።
በውይይት መድረኩ የተገኙ የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ በላይ ተሰማ የፖለቲካ ትርጉም ተሰጥቶ ህብረተሰቡን በማነቃነቅና የባለድርሻ አካላትን በተገቢው በማሳተፍ ከተሰራ እንደ ክልል በጤና ዘርፍ ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል ብለዋል።
ተገቢ የህክምናና የወለድ አገለግሎት በተገቢው ሰዓትና ቦታ እንዲሁም በሰለጠነ ባለሙያ በመስጠት አብዛኛውን የእናቶችና የጨቅላ ህፃናት ሞት ለመቀነስ በክልሉ በሁሉም አከባቢ የእናቶች ማቆያ ቤት እንዲኖር በፍጥነት ሊሰራ ይገባል ተብሏል።
በየደረጃው የሚገኙ የጤና ተቋማትና የአስተዳደር አካላት የወቅቱን የገበያ ሁኔታና የህብረተሰቡን የመድኃኒት ዋጋ ታሳቢ ያደረገ ተገቢ የመድኃኒት መግዣ በጀት ሊመድቡ እንደሚገባ በአፅንኦት ተነስቷል።
ከአምቡላንስ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በክልሉ የሚስተዋለውን ሰፊ ክፍተት ለመፍታት ከጤና ቢሮ ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ያሉ የዘርፉ የባለድርሻ አካላት ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል የጉባኤው ተሳታፊዎች።
የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራና ልየታ እንዲሁም የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ተግባራት በልዩ ትኩረት ሊከናወኑ የሚገቡ ጉዳዮች እንደሆኑም ተነስቷል።
ምንጭ፡ የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ