በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ22 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ኩንታል አትክልትና ስራስር በመስኖ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ

በክልሉ እየተካሔደ ያለው የአትክልትና ስራ ስር ልማት የአምራቹንና ሸማቹን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግም ተጠቁሟል፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንደገለጹት በተያዘው የምርት ዘመን ከ103 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በማረስ ከ22 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል አትክልትና ስራስር በመስኖ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ በበጋና በበልግ የአዝመራ ወቅት እየለማ ያለው አትክልት እና ስራስር የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት ስኬታማ ያደርጋል ብለዋል።

በሁሉም ዞንና ልዩ ወረዳ ባሉ ቀበሌያት በመስኖ እየለማ ባለው አትክልትና ስራስር ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ ነው ያሉት አቶ ኡስማን በመስኖ የተጀመረውን የአትክልት ልማት በበጋው ወቅት የበለጠ በማስፋት የአምራቹንና እና የተጠቃሚውን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በክልሉ ያለውን ፀጋ በማልማት የአምራቹን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ የገበያውን የአቅርቦት ክፍተት በመሙላት የሸማቹን ችግር መፍታት ያስፈልጋል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

በበጋና በዘንድሮው የበልግ ወቅቶ የተቀናጀ የግብርና ልማት ስራዎችን ለማከናወን ከተቀመጡ ግቦች መካከል የአትክልትና ስራስር ልማት ስራዎች ተጠቃሽ መሆኑንም አስታውሰዋል።

የየአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ አትክልት ማልማት በትንሽ መሬት ለአምራቹ ከፍተኛ ምርትና ገቢ የሚያስገኙ እና የኑሮ መሻሻል፣ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር፣ በገበያ ውስጥ ያለውን የአቅርቦት ክፍተት በመሙላት እና ከግብአት አቅርቦት እስከ ገበያ ባለው ሂደት ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ከፍ ያለ ሚና እንዳለውም ኃላፊው አብራርተዋል።

በተለይም ለሴቶች እና ለወጣቶች የልማት ተሳትፎና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መረጋገጥ የላቀ ሚና እንዳለውም አቶ ኡስማን መናገራቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ያሳያል።