የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል

በመርሀ ግብሩ መክፈቻ ላይ የሊጉ ፕሬዚዳንት ወጣት አክሊሉ ታደሰ የሊጉ ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት አባንግ ኩመዳን የዘርፉ ምክትል ሀላፊ  አቶ ፓል ቱት እንዲሁም የወጣቶች ሊግ ስራ አስፈፃሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል።

ኮሚቴው በ3 አጀንዳዎች ላይ ውይይት የሚያደርግ ሲሆን የመዋያያ ርዕሰ ጉዳዮችን በአብላጫ ድምፅ በማፅደቅ በይፋ መድረኩ ተጀምሯል።

የኮሚቴውን ቆይታ በመክፈቻ ንግግር የከፈቱት የሊጉ ፕሬዚዳንት ወጣት አክሊሉ ታደሰ ሊጉ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማስፋት ስትራቴጂክ ሀሳቦች እና የለውጥ ምህዋሮች የሚዘወርበት እንዲሆን ሰፊ ስራዎችን እንደተሰሩ አንስተዋል።

በተለይም ባለፉት 6 ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጣቶችን የማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ልህቀት በተላበሰ ደረጃ ለማሳደግ ተግባራዊ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ እንደነበሩ ገልፀዋል።

በመርሀ ግብሩ ላይ በሊጉ ምክትል ፕሬዚዳንት በወጣት አባንግ ኩመዳን የሊጉ የ6ወራት አፈፃፀም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ከእቅድ ዝግጅት እስከ ትግበራ ምእራፍ የነበሩ የአፈፃፀም ሂደቶች ተዳሰዋል።

በዚህም በበጎፍቃድ እንቅስቃሴዎች፣በንቅናቄ ተግባራት፣የሚሰጡ ወቅታዊ ተልእኮዎችን በመፈፀም፣በሀገራዊ ተልእኮዎች ወጣቶችን በማስተባበር ረገድ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸው ተነስቷል።

በሊጉ እና በዋና ፓርቲው ጉባኤዎች የተላለፉ ውሳኔዎች በአግባቡ ተፈፃሚ እንዲሆኑ የተደረጉ ጥረቶች ፍሬያማ እንደነበሩ እና በቀጣይም የታዩ ክፍተቶችን ለማረም ምልአተ ወጣቱን በማስተባበር ሰፋፊ ስራዎች መሰራት እንደሚገባቸው ተጠቅሷል።

የማእከላዊ ኮሚቴው ቆይታ ለተከታታይ 2 ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ውይይቶች የተሞክሮ ልውውጥ መድረኮች እንዲሁም ለቀጣይ የስራ አቅጣጫ አቅም መፍጠር የሚችሉ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉበት ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።