ጥራት ያለው የጤና አገለግሎት ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥር 25/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ጥራት ያለው የጤና አገለግሎት ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን የጤና ሁኔታ ለማሻሻል የሁሉም የባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የግማሽ አመት የጤና ተግባራት አፈፃፀም ግምገማ ጉባኤ በታርጫ ከተማ በመከናወን ላይ ይገኛል።

በጉባኤ የተገኙ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ጥራት ያለው የጤና አገለግሎት ተደራሽ በማድረግ የማህበረሰቡን የጤና ሁኔታ ለማሻሻል የሁሉም የባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበዬሁ በበኩላቸው የመድኃኒትና የጤና ግብአት አቅርቦት ተደራሽነት ለማሻሻል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

ጉባኤው በባለፉት ስድስት ወራት በጤና ዘርፍ የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶችን አጠናክሮ ማስቀጠልና በጉድለት የተገመገሙ ጉዳዮችን ማሻሻልን አላማ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በጉባኤው የክልል፣ የዞኖች፣ የወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት  ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ አባይነሽ ወራቦ- ከዋካ ጣቢያችን