ባለፉት ስድስት ወራት በሁሉም የግብርና ዘርፎች ስኬቶች ተመዝግበዋል- ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)

ሀዋሳ፡ ጥር 25/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ባለፉት ስድስት ወራት እንደ ሃገር  በሁሉም የግብርና ዘርፎች ትላልቅ ስኬቶች መመዝገባቸውን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ተናገሩ።

የግብርና ሚኒስቴር ፣ ተጠሪ ተቋማትና የክልሎች የ2016 በጀት የመጀመሪያው ግማሽ አመት የስራ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በአርባ ምንጭ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር  በሁሉም የግብርና ዘርፎች ባለፉት ስድስት ወራት የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል።

በተለይ በበልግ እርሻ ወቅት ጥሩ የሚባል ጊዜን ማሳለፍ እንደተቻለና በአነስተኛ ማሳ ጭምር 17 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መልማቱን ጠቅሰዋል።

በመስኖ ልማት ሥራም ባለፉት ሁለት እና ሶስት ወራት ወደ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አብራርተዋል።

በሌማት ትሩፋት ፣ በአረንጓዴ አሻራ ፣ እንዲሁም  ከማዳበሪያ ግዢና ስርጭት ጋር ያሉ አፈጻጸሞች መልካም ስለመሆናቸው አንስተዋል።

በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አፈጻጸምን ጨምሮ የሌሎች ብሄራዊ ክልሎች የዘርፉ አፈጻጸም እየቀረበ ነው።

ዘጋቢ፡  ወንድወሰን ሽመልስ