ሀዋሳ፡ ጥር 25/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዞኑ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ የዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አሳሰበ።
መምሪያው በ2016 ዓ.ም የመጀመሪያ ግማሽ አመት አፈጻጸምና ዞን አቀፍ ምዘና አሰጣጥን ውጤታማ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ግምገማ ነክ የውይይት መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደ ማርያም በዚህ ወቅት እንደገለፁት በዞኑ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ የዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ሁሉን አቀፍ ንቅናቄ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና መጫወት ይገባቸዋል።
የዞኑ ማህበረሰብ ለትምህርት ዘርፉ እድገት እያበረከተ ያለው ኢኮኖሚያዊና የቁሳቁስ ድጋፍ ከፍተኛ ነው ያሉት ኃላፊው ይህንን እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ለመማር ማስተማሩ ሂደት የሚያስፈልጉ ግብአቶችንና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በዞኑ አዲሱ ስርአተ ትምህርትን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ የመማሪያ መፃህፍት አለመሟላት ከፍተኛ ተግዳሮት እየሆነ ይገኛል ያሉት አቶ መብራቴ ችግሩን ለመቅረፍ ወላጆችንና ባለሀብቶችን ያሳተፈ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ በመዘርጋት መፃህፍቶቹን ለማሳተም እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ይህንን በመገንዘብ የየመዋቅሩ አመራሮችና ወላጆች ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሀብት የማሰባሰብ ዘመቻው ውጤታማ እንዲሆንና ተማሪዎች የመማሪያ መፃህፍት አግኝተው በየደረጃው በሚሰጡ ምዘናዎች ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እገዛ ማድረግ እንዳለባቸው ኃላፊው አስረድተዋል።
በጥሩ ስነምግባርና ክህሎት የታነፁ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት የትምህርት ተቋማት በፈጠራና ምርምር ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ያሉት አቶ መብራቴ ዞኑ በዘርፉ ያለውን ምርጥ ተሞክሮ ይበልጥ ለማስፋትና የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማበረታታት ልዩ መርሃ ግብር ቀርፆ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ በዞኑ በ341 የቅድመ መደበኛ ጣቢያዎች የጉራጊኛ ቋንቋ ትምህርት አሰጣጥ ተግባራዊ መደረጉን ያስረዱት ኃላፊው በአተገባበሩ የታዩ ውስንነቶች ተቀርፈው ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን የተለየ ክትትልና ድጋፍ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ የመድረኩ ተሳታፊዎችም የምክክር መድረኩ ያሉባቸውን ጉድለቶች ለይተው በቀጣይ ህብረተሰቡን በንቃት በማሳተፍ የመፍትሄ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
የመረጃ ፍሰት ወጥ አለመሆን፣ የመምህራን ፍልሰት መበራከት፣ የተማሪ መጠነ ማቋረጥ ማሻቀብ፣ የመማሪያ ግብአት አለመሟላትና ሌሎችም ተያያዥ ችግሮች በመድረኩ በውስንነት የተገመገሙ ሲሆን በቀጣይ መሻሻል በሚገባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ የመፍትሄ አቅጣጫ ተቀምጦላቸዋል።
ዘጋቢ፣ አስቻለው ተስፋዬ- ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ