የፍርድ ቤቶች የሪፎርም ፍኖተ ካርታ በተቋሙ ብልሹ አሰራሮችን የሚቀርፍ  መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥር 25/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የፍርድ ቤቶች የሪፎርም ፍኖተ ካርታ በተቋሙ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን የሚቀርፍ  መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለድርሻ አካላት ገለጹ።

በዞኑ ፍርድ ቤቶች የሪፎርም ፍኖተ-ካርታ ሰነድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሆሳዕና ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

የሀዲያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ጥላሁን ዴታሞ ባደረጉት ንግግር መንግስት የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ ለማድረግ በርካታ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡ይህ ቢሆንም የሕብረተሰብን ፍላጎት በሚያረካ ደረጃ ማድረስ አለመቻሉን ገልጸዋል።

በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሪፎርም ፍኖተ ካርታ ተቀርጾ ወደ ትግበራ እየተገባ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ጥላሁን ፍኖተ ካርታው ተጠያቂነትን የሚያሰፍን በመሆኑ ችግሮቹ በዘላቂነት ይፈታል የሚል እምነት እንዳለቸው ተናግረዋል።

በዕለቱ የሪፎርም ፍኖተ ካርታ ሰነድ በባለሙያ የቀረበ ሲሆን ተሳታፊዎችም ሰነዱን መነሻ በማድረግ ተወያይተዋል።

ሕብረተሰብን በቅንነት አለማገልገል፣ ቀጠሮ ማብዛት፣ በዝምድና ፍትህ ማዛባት እና እጅ መንሻ መፈለግ፣ በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ናቸው ሲሉ የመድረኩ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

ሪፎርሙ ክፍተቶቹን በመሙላት ሕብረተሰቡ ከዘርፉ ተገቢ አገልግሎት እንዲያገኝ ይረዳል የሚል እምነት እንዳለቸውም ነው የተናገሩት፡፡

የሀዲያ ዞን ዋና አፈ-ጉበኤ ወ/ሮ እቴነሽ ሙሉጌታ ፍኖተ ካርታው በፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉትን ዘረፈ ብዙ ችግሮች በመፍታት የተገልጋዩን ሕብረተሰብ ዕንግልት የሚቀርፍ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሪፎርሙ ግቡን እንዲመታ ምክር ቤቱ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም ተናረዋል፡፡

ዘጋቢ ፡ ጌታቸው መጮሮ-  ከሆሳዕና  ጣቢያችን