ሀዋሳ፡ ጥር 25/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በወልቂጤ ዩኒቨርስቲና በሠላም ሚኒስቴር ትብብር የተዘጋጀ የውይይት መድረክ “አድዋን ለዘላቂ ልማትና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል::
በመድረኩ ላይ የተገኙት በሠላም ሚኒስቴር የመንግስታት ግንኙነት ዴስክ ሀላፊ አቶ ግርማ ቸሩ እንደተናገሩት የአድዋ ድልን መዘከር በየትኛውም መስክ ለተሰማራው ዜጋ፣ ለሀገር ሁለንተናዊ ልማት፣ ሠላምና ዘላቂ እድገት በአድዋዊ የአንድነትና የድል አድራጊነት መንፈስ እንዲተጋ የማነሳሳት ፋይዳ አለው::
ኃላፊው አክለውም የአድዋ ድል ለመላው አፍሪካዊያንና ለጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት መሆኑን ገልፀዋል::
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፉሪስ ደሊል በበኩላቸው በቀደምት ጀግኖች አባቶች ከተገኘው ድል አዲሱ ትውልድ የአንድነት መንፈስን በመማር ውስጣዊ ችግሮችን በምክክር መድረክ በመፍታት በኢትዮዽያ ዘላቂ ሠላም፣ ልማትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል::
በውይይት መድረኩ የአድዋ ታሪካዊ ገጽታ፣ የሀገርና ሀገረ መንግስት ግንባታና እሴቶች ላይ ያተኮሩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ ጥናታዊ ጽሁፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል::
ከጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢዎች መካከል በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ በቃሉ ዋቺሶ እንደገለፁት በጀግና አባቶች ደም የተገኘውን የድል ፍሬ ይህ ትውልድም ድሉን በተግባር ማስቀጠል ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡
በምክክር መድረኩ በቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎች ላይ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ በቀረቡ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸው የውይይት መድረኩ ተጠናቋል::
ዘጋቢ፡ መሀመድ ጀማል
More Stories
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቅን ምክንያት በማድረግ የይርጋጨፌ ወረዳ እና ከተማ አስተዳደር በጋራ በመሆን የድጋፍ ሰልፍ አካሄዱ
ሙያዊ ስነ-ምግባር የተላበሰ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ
የካፋ ዞን ጤና መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2018 ዕቅድ ዝግጅት ላይ ውይይት እያካሄደ ነው