ለህፃናት አስፈላጊ ድጋፍና ክትትል ጥበቃና እንክብካቤ ተግባር ላይ የሚዉል ከ34 ሚሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ ፕሮጀክት በአርባ ምንጭ ከተማ ይፋ ሆነ
ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
ማህበረሰብ ለማህበረሰብ የህፃናት መንደር ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ138 በላይ ሀገራት ውስጥ የሚሰራና እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1945 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በኢትዮጵያ ሥራውን ከጀመረ 50 ዓመታትን አስቆጥሯል ተብሏል።
በፕሮጀክቱ ማብሰሪያ መርሀ ግብር ላይ የተገኙት የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ፤ ፕሮጀክቱ የህፃናትን የወደፊት ተስፋ ለማለምለም እያደረገ ያለውን ተግባር አድንቀዋል።
በአርባ ምንጭ ከተማ በህፃናት አስተዳደግና ተያያዥ ችግሮች ላይ በሰፊው መሰራት እንዳለበት የጠቆሙት ከንቲባው፤ ፕሮጀክቱ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ሥራው በአርባ ምንጭ ከተማ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ተግባራዊ ይሆናል ያሉት የማህበረሰብ ለማህበረሰብ የህፃናት መንደር አርባ ምንጭ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዳግማዊ ተሾመ፤ ፕሮጀክቱ በከተማው በተመረጡ ሁለት ቀበሌያት 635 ቤተሰቦችን መሠረት በማድረግ 110 ሺህ 80 ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በትምህርት፣ አስቸኳይ እርዳታ፣ በወጣቶችና በጤናው ዘርፍ የሚሰራ መሆኑን አውስተው፤ የቤተሰብ ጥበቃና እንክብካቤ ያጡና ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ህፃናት መብታቸው ተጠብቆ መኖር እንዲችሉ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ተግባር እንደሚያከናውንም አክለዋል።
ወላጆች አቅም ግንባታ ላይም እንደሚሰራ የተናገሩት ኃላፊው ፕሮጀክቱ 34 ሚሊዮን 2 መቶ 90 ሺህ ብር እንደሚፈጅ አብራርተዋል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፋ ባለድርሻ አካላት ፕሮጀክቱ የያዘውን ዓላማ እውን እንዲያደርግ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን ብለዋል።
ዘጋቢ፡ አማሮ አርሳባ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሙዱላ ከተማ አስተዳደር ገለፀ
በትምህርት ሴክተር የመረጃ አያያዝ ውጤታማነት ዙሪያ በኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
ሁሉንም የመማሪያ መጻሕፍት ባለማግኘታቸው በትምህርታቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የቆንጋና ቆቄ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ