የአሁኑ ትውልድ የራሱ ባህልና ወግ ጠንቅቆ በማወቅ በባህልና እሴቱ እንዲኮራና ለባህል ወረራ እንዳይጋለጥ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ተገለፀ
የአሁኑ ትውልድ የራሱ ባህልና ወግ ጠንቅቆ በማወቅ በባህልና እሴቱ እንዲኮራና ለባህል ወረራ እንዳይጋለጥ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
ይህ የተገለፀው “አንትሮሽት” ወይም የእናቶች የምስጋና አመታዊ ክብረ በዓል በጉራጌ ዞን በጉመር ወረዳ በድምቀት በተከበረበት ወቅት ነው።
በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ እንዳስታወቁት በክልሉ ነባርና ሀገረሰባዊ ባህሎች ጎልተው እንዲወጡ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በየአካባቢው እየጠፉ ከሚገኙ ነባርና ጠቃሚ የሆኑ ባህላዊ እሴቶች መካከል አንትሮሽት ወይም የእናቶች የምስጋና በዓል አንዱ ነው ብለዋል ሀላፊው።
በመሆኑም ይህንኑ አኩሪ እሴት ጠብቆ በማቆየት ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ በማንሳት በዓሉ ከጉራጌ ዞኖች አልፎ በሀገር ደረጃ የሚያበረክተው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ በቀጣይ በማልማትና በማስተዋወቅ የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ቢሮው በትኩረት ይሰራልም ነው ያሉት፡፡
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንደተናገሩት እንደ ሀገር ቀድመን የጀመርናቸው ባህላዊ እሴቶች በአግባቡ መልማት ባለመቻላቸው ህብረተሰቡ ከዘርፉ ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል።
ስለሆነም የአሁኑ ትውልዱ ባህሉና ወጉን ጠንቅቆ በማወቅ በራሱ ባህልና እሴት እንዲኮራና ለባህል ወረራ እንዳይጋለጥ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ነው የገለፁት፡፡
በዓሉ በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ እናቶች በህይወት ዘመናቸው ላበረከቷቸው አስተዋጽኦዎች ባሎቻቸውና ልጆቻቸው የተለያዩ ስጦታዎች በመስጠት እንዲያመሰግኑ ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ገልፀው በቀጣይም ይበልጥ በማልማትና በማስተዋወቅ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ነጅሚያ መሀመድ በበኩላቸው በዓሉ እናቶች በልጆቻቸውና በማህበረሰቡ ዘንድ እንዲከበሩና የድካማቸው ዋጋ እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥ ባለድርሻ አካላት አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በዓሉ እንዲያንሰራራና ከዞኑ አልፎ በሀገርና በአለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ የዓለም ቅርስ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊዋ አስረድተዋል፡፡
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት አመርጋ በባለፉት ዓመታት የበዓሉ አከባበር ላይ መቀዛቀዝ አንደነበረ ጠቁመው አሁን ላይ ለውጦች መኖራቸውንና በቀጣይ በተሻለ ሁኔታ እንዲከበርም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራልም ነው ያሉት።
የበዓሉ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም አንትሮሽት/የእናቶች የምስጋና ቀን/ በደመቀ ሁኔታ በመከበሩ መደሰታቸውን በመግለፅ በእለቱ ከስራ ሁሉ ነፃ ሆነው የሚያርፉበት፣ በልጆቻቸውና በባለቤቶቻቸው የሚከብሩበትና የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች በማዘጋጀት እንዲደሰቱ የሚደረግበት እለት መሆኑን ተናግረዋል።
የእናቶች የምስጋና ቀን በቀጣይ በተሻለ መልኩ እንዲከበር በየደረጃው እየተደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
ዘጋቢ፡ መሃመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ