የኮሬ ዞን፣ የኬሌ ከተማ አስተዳደር፣ የወረዳዎች ከፍተኛ አመራሮችና የሐይማኖት አባቶች፣ የዋርካ አግሮ ኢንዱስትሪን ጎበኙ

ሀዋሳ፡ ጥር 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኮሬ ዞን፣ የኬሌ ከተማ አስተዳደር፣ የወረዳዎች ከፍተኛ አመራሮችና የሐይማኖት አባቶች፣ የዋርካ አግሮ ኢንዱስትሪን ጎብኝተዋል።

የዋርካ አግሮ ኢንዱስትሪ በዞኑ ኬሌ ከተማ በእንቁላል ጣይ ዶሮ ዘርፍ ተሰማርቶ ለሌሎች አርዓያ የሚሆን ተግባር እየፈጸመ ያለ ማህበር ነው።

በጉብኝቱ ላይ የዋርካ አግሮ ኢንዱስትሪ ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ እምነቱ አድነው እንደገለጹት፣ ከዩቲዩብ ተሞክሮዎችን በማየት 1ሺህ 2 መቶ ዶሮዎችን በቅርቡ በማስመጣት አሁን ላይ ምርት መስጠት በመጀመራቸው በቀን አምስት መቶ በላይ እንቁላሎችን እያገኙ ናቸው።

ሥራ አስኪያጁ ለጎብኝዎች እንደገለጹት፣ በሌማት ትሩፋቶች ውጤታማ የሚሆኑበትን ፕሮጀክት ቀርጸዋል።

በዞኑ ማህበሩን የሚደግፉ የዶሮ እርባታ ባለሙያ አክሊሉ አምዛዬ፣ የዶሮ መዋያ በተገቢው መንገድ ከተዘጋጀ አካባቢው ለዶሮ እርባታ ምቹ ነው ብለዋል። በዋርካ አግሮ ኢንዱስትሪ ያሉ ዶሮዎች እንቁላል መሥጠት መጀመር ከነበረባቸው ሳምንት ቀድመው መጀመራቸው  ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።

የጎርካ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አገኘሁ በቀለ፣ ያዩትን  ወደሌሎች የወረዳው ቀበሌዎች የሚያሰፉ መሆኑንና ሌሎች ወጣቶች እንዲጎበኙ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

የኮሬ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ በቀለ በጉብኝቱ ወቅት የማህበሩ ተሞክሮ አስደሳች ነው ብለው አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

እንደዞን መንግስት ተሞክሮውን ወደሌሎች ወጣቶች ለማስፋት ይሰራል ብለው፣ በአስፈላጊ ነገሮች ዞኑ አግሮ ኢንዱስትሪ ማህበሩን የሚደግፍ ይሆናል ነው ያሉት።

ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን