የጌዴኦ ባህላዊ መልከአ ምድር በዮኔስኮ የዓለም ቅርስነት መመዝገብ ዕዉቅና አሰጣጥ ፕሮግራም ተካሄደ

ሀዋሳ፡ ጥር 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጌዴኦ ባህላዊ መልከአ ምድር በዮኔስኮ የዓለም ቅርስነት መመዘገብን በማስመልከት የዕዉቅና አሰጣጥና አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የሽልማት ፕሮግራም በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ በጨልባ ቱቲቲ የባህል ቅርስ ተካሂዷል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ዝናቡ ወልዴ በዕዉቅና አሰጣጥ ፕሮግራም መድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር አንዳሉት፤ የጌዴኦ ህዝብ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንግስት አስተዳደር ከመመስረቱ በፊት በባሌ ስርዓት ይተዳደር የነበረ ህዝብ እንደሆነና በባሌ ባህላዊ የአስተዳደር ስርዓት አሁንም ድረስ ህዝቡ የሚተዳደርበት መሆኑን ጠቅሰው በስርዓቱ የሰው ልጆች ከዕፀዋት ጋር አብሮ እንዴት ሊኖሩ እንደሚገባ በግልፅ አስቀምጧል።

የጌዴኦ ጥምር ድብልቅ የእርሻ ዘዴ ዓለም የሚማርበት፣ ለዓለም የአየር ንብረት መጠበቅ ጉልህ አስተዋፅኦ ያለው፣ የጌዴኦ ህዝብ ሀገር በቀል በሆነው ሥርዓቱ ተንከባክቦ የጠበቀው ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

የጌዴኦ ህዝብ ጠብቆ ያቆየውን ቅርስ ለመጪው ትዉልድ ጠብቆ እንደሚያቆይ አረጋግጠዋል።

የተመዘገበው ቅርስ ኢኮኖሚ የሚያመነጭ መሆኑን በመገንዘብ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በቀጣይም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመስራት ማስቀጠል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ቅርሱን ጠብቀው ለትውልድ ያቆዩ አባቶችን በማመስገን ለጌዴኦ ህዝብና ለሁሉም አካላት እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፍሬህይወት ዱባለ በበኩላቸው የጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር ቅርስ ዩኔስኮ ህዳር 17/2016 ዓ.ም በሳውዲ አረቢያ ሪያድ ከተማ ባካሄደው 45ኛው የዓለም ቅርስ ኮሚቴ ስብሰባ ቅርሱ በዩኔስኮ የዓለም ዝርዝር እንዲመዘገብ በመወሰኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከተሰጡት ተግባርና ኃላፊነቶች አንዱና ዋነኛው በክልሉ የሚገኙ ቅርሶችን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ማሰስ፣ መለየት፣ መመዝገብ፣ ማጥናትና ማልማት ነው ብለዋል፡፡

ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር ዕጩ የዓለም ቅርስ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከፌደራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣንና ከጌዴኦ ዞን አስተዳደር ጋር ለማስመዝገብ ቢሮው በርካታ ስራዎችን ሰርቶ ለዚህ ድል መብቃቱን አብራርተዋል፡፡

ቅርሱ በዓለም ቅርስነት ሲመዘገብ የሰው ልጅ የስራና የተፈጥሮ ሂደት የጋራ ውጤት በመሆኑ እንደሆነ ኃላፊዋ አንስተዋል፡፡

የጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር ቅርስ ጤናማና ዘላቂነት ያለው የምግብ ልዕልናነን ለማረጋገጥ፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለዓለም አየር ንብረት መጠበቅ የላቀ ጠቀሜታ የሚሰጥ በመሆኑ በዘላቂነት ጥበቃውን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ቅርሱ የረጅም ዘመናት የአኗኗር፣ የሀገር በቀል እውቅት እንዲሁም የተፈጥሯዊ ሂደትና የሰው ልጅ ስራ ውጤቶች በመሆኑ ይህንን የዓለም ቅርስ ለመጪው ትውልድ ጠብቆና ተንከባክቦ ማቆየት የሁሉም ድርሻ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

የፌደራል፣ የክልልና የዞኑ ተቋማት፣ የተለያዩ ምሁራን ያላሰለሰ ጥረታቸውን በማድረግ ምዝገባው የትጋታችሁ ውጤት በመሆኑ በሂደቱ ለተሳተፉ፣ ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን ለሰጡ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በዕዉቅና አሰጣጥ ፕሮግራሙ ላይ የፌደራል ቅርስ ባለስልጣን አካላት እና ሚኒስትር ዴኤታ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፣ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ፍሬህይወት ዱባለ፣ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ዝናቡ ወልዴ እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ብዙነሽ ዘውዱ