ሀዋሳ: ጥር 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከተፈጥሮ የምንፈልገውን ያህል ጥቅም ማግኘት የምንችለው ተገቢውን እንክብካቤና ጥበቃ በማድረግ ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ተናገሩ::
ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው “የተፈጥሮ ሀብትን ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል የተካሄደውን የዘንድሮውን ክልል አቀፍ የተፋሰስ ልማት ሥራ በጠምባሮ ልዩ ወረዳ በይፋ አስጀምረዋል::
ተፈጥሮ እንደ ልጅ እንክብካቤን የሚሻ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው የምፈለገውን ጥቅም ከተፈጥሮ ለማግኘትም ተገቢው ጥበቃና ክብካቤ አስፈላጊ ነው ብለዋል::
የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ ኢኮኖሚውን ከሚገነቡት ቀዳሚው ግብርና ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የአካባቢ ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ሥራ ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስገንዝበዋል::
የአፈር ለምነትን በመጨመር ምርታማነትን ለማሳደግም ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል::
ኢትዮጵያውያን የምንከበረው ግብርናችንን ስናለማ፣ ምርታማነትን ስናሳድግ እና እራሳችንን በምግብ ስንችል ነው ሲሉ አብራርተዋል::
ባለፉት ጥቂት አመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጠንካራ አመራር ሰጪነት በስንዴ ልማት ላይ የተደረገው ከፍተኛ ርብርብ ትልቅ ውጤት የተመዘገበበት እና እንደ ሀገር ከውጭ ይገባ የነበረውን የስብዴ ምርት ማስቀረት የተቻለበት ነው::
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ለስንዴ ታወጣ የነበረውን ቢሊዮን ዶላር ያስቀረ ከመሆኑም በላይ ወደ ሌሎች ሀገራት በመላክ ላይ እንደምትገኝም ገልጸዋል::
መሰል ተስፋ ሰጪ ሀገራዊ የምርታማነት ሥራችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ የሚኖረውን ትልቅ ሚና ከግንዛቤ በማስገባት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል::
በክልሉ ከ147 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የተፈሰስ ልማት ሥራ እንደሚከናወንበት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ገልጸዋል::
ቀደም ባሉት አመታት በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥዎች ምንጮች እየጎለበቱ መምጣታቸውን እና ደኖች እየተስፋፉ መሆናቸውን አስታውቀዋል::
ለበርካታ አርሶ አደሮች ምርታማነት እና ገቢ ማደግ ትልቅ ድርሻ እያበረከተ ይገኛልም ብለዋል::
የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት፣ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ሥራዎች፣ የበልግ እርሻ ልማት ሥራ፣ የበጋ አትክልት ልማት፣ የእንስሳት ልማት እና የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራዎችም ጎን ለጎን የሚከናወኑ የትኩረት ነጥቦች መሆናቸው ተገልጿል::
የተፈጥሮ ጥበቃ ሥራ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ቀስቃሽ የሚያሻው አይደለም ያሉት ደግሞ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ ናቸው::
ተግባሩ የሁላችንም ጉዳይ በመሆኑም በኃላፊነት ስሜት መወጣት እንደሚገባም አሳስበዋል::
የጠምባሮ ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አበራ ሀርፍጮ በበኩላቸው ልዩ ወረዳው ከሶስት ክልሎች ጋር አዋሳኝ በሆነ ሥፍራ ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የሥነ ምህዳር ልማትን በማፋጠን ለጋራ ተጠቃሚነት የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል::
የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ለቀጣይ 22 ቀና በልዩ ወረዳው ይከናወናል::
ዘጋቢ፡ ማሬ ቃጦ
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ