የህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት ለሟሟላት እየተሰሩ ያሉት ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

ሀዋሳ፡ ጥር 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት ለሟሟላት እየተሰሩ ያሉት ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ይህ የተባለው የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የ6 ወራት አፈጻጸሙን ከክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

ባለፉት 6 ወራት ውስጥ 11 የከተማ እና 591 የገጠር አዳዲስ መጠጥ ውሃ ጥናትና ዲዛይን ለማዘጋጀት ታቅዶ በከተማ 8፣ በገጠር ደግሞ 357 ማከናወን መቻሉን የቢሮው ምክትል ኃላፊና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳንቴሽን ዘርፍ ሀላፊ ኢንጅነር ፈልታሞ ድብሎ አስረድተዋል፡፡

ለ10 ነባር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የዲዛይን ማሻሻያ ሥራዎችን ለማከናወን ታቅዶ 11 የተከናወነ መሆኑን የገለጹት ኢንጅነር ፈልታሞ በዚህም 40 ሺህ የከተማና የገጠር ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

የቦንጋ ከተማ ንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር መፍትሔ ከመሻት አኳያ በተደረገዉ ርብርብ 13 ሺህ የሚሆኑ የከተማ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉም ተጠቁመዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ እንዲቻል በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜያት ለመቅረፍ የጥናትና ዲዛይን ስራ እየተከናወነ ሲሆን የጥናቱ ውጤት 50 ከመቶ በላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡የሚዛን አማን ደግሞ ሙሉ በሙሉ ስለመጠናቀቁ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

10 በተለያዩ ፕሮግራሞች እየተገነባ የሚገኘዉ የመስኖ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች የክትትልና ቁጥጥር ስርዓቱን በማጠናከር ግንባታዉን ለታለመለት ዓላማ ማዋል እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን 69 ነባር የመሰኖ ውሃ ተጠቃሚ ማህበራት ላይ የማጠናከሪያ ሰራ እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ቢሮው 2 የአቅመ ደካማ ማህበረሰብ የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት አቅዶ በቦንጋ ከተማና በአመያ ከተማ አስተዳር 2ቱን ማከናወን የተቻለ መሆኑንና ለ5 አቅመ ደካማና አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ድጋፍ መደረጉ በሪፖርቱ ቀርቦ በቋሚ ኮሚቴው ተገምግሟል፡፡

ህገ-ወጥ የወርቅ ግብይትን ለመከላከል የክልሉ መንግስት ግብረ-ሀይል አቋቁሞ በሰራቸው ሰራዎች መሻሻሎች የታዩ ቢሆንም በየደረጃው የሚገኙ የማዕድን ተቋማት ሰራውን በባለቤትነት በመሰራት ላይ ክፍተቶች መስተዋሉን በሪፖርት ተካቷል፡፡የቢሮ ጥበት፣ በዞኖች የግንባታ ቁጥጥር እና ኮንትራት አሰተዳደር ስራ ደካማ መሆን፣ የስራ ተቋራጮች አቅም ውሰንነት፣ የግንባታ ግብአቶች ዋጋ መናርና የሰው ሀይል እጥረት በአፈጻጸም ወቅት የታዩ ማነቆች ናቸው ተብሏል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢው አቶ አዲስምዕራፍ ዓለሙ እንደገለጹት የክልሉን ህብረተሰብ የዘመናት የልማት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

በአፈጻጸም ወቅት የተስተዋሉ ችግሮች እንዲቀረፉ በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አቶ አዲስምዕራፍ አሳስበዋል፡፡

የውሃ ፕሮጀክቶች በክልሉ 6ቱም ዞኖች በክልሉና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት የቢሮ ሀላፊ ኢንጅነር በየነ በላቸው ግማሽ ቢሊዮን በሚጠጋ ብር ወጪ ተደርጎ የግንባታ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

በካፋ ዞን ዋቻ ከተማ፣ በሸካ የገቲባ ቀበሌና በዳዉሮ ዞን የታርጫ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በቅርቡ እንደሚመረቁ ኢንጂነር በየነ በላቸው ገልጸዋል፡፡

ባለፉት 6 ወራት በተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ ከቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት የተሰጠውን አስተያየት በቀጣይ የተቋሙ ዕቅድ አካል በማድረግ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ በየደረጃው የሚገኘው አካል ሚናውን እንዲወጣ ኢንጂነር በየነ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ብዙአየሁ ጫካ – ከቦንጋ ጣቢያችን