የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት በሰዎች መነገድና ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን በተመለከተ ለክልሉ የዳኝነትና ፍትህ አካላት  ስልጠና እየሰጠ ነው

ሀዋሳ፡ ጥር 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት በሰዎች መነገድና ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን በተመለከተ ለክልሉ የዳኝነትና ፍትህ አካላት  ስልጠና እየሰጠ ነው።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በክልላችን በተለያዩ አካባቢዎች በሴቶችና ህጻናት የወደፊት ዕድል ፈንታቸው ላይ የሚፈጸም ህገ ወጥ ተግባር ለከፋ እንግልትና ስቃይ እያጋለጠ መጥቷል ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከግል ተበዳዮች አልፎ በሚኖሩበት ማህበረሰብም ላይ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ጠቅሰው የፍትህ አካላት ጥቃቱ እንዳይፈጸም  አስቀድሞ በመከላከል፣ ተፈጽሞም ሲገኝ ጥቃት አድራሹ በህግ እንዲጠየቅና አስተማሪ ቅጣት ማግኘት እንዲችል መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ ፍትህና ህግ  ኢንስቲትዩት ዋና ዳይረክተር አቶ አባይነህ አደቶ በበኩላቸው በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ከአገር የማስወጣት ወንጀል በአገር ደረጃም ሆነ በክልሉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ወንጀል ነው ብለዋል።

ወንጀሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩንና ባህሪውን እየቀየረ የመጣ  በመሆኑ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻልም መጠኑን ለመቀነስ ኢንስቲትዩቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለክልሉ ዳኞ፣ ዓቃቢያነ ህጎች፣ መርማሪ ፖሊሶችና ባለድርሻ አካላት በወንጀሉ ጽንሰ ሀሳቦች፣ ስለ ህግ ማዕቀፎች፣ ስለ ወንጀል ምርመራ ክስና ክርክር ሂደት እንዲሁም ተጎጂዎችን መልሶ ስለማቋቋምና በፍትህ አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መካከል ሊኖር ስለሚገባው ቅንጅታዊ አሰራር ግንዛቤ ለመፍጠር  ስልጠናው መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ወንጀሉ የሚፈጸመው በተደራጀ የወንጀል ቡድኖችና በተናጠል የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት አቅደው በሰው ልጆች ስቃይና ደም ከፍተኛ ጥቅም የሚያገኙበት አደገኛ ወንጀል ነው ብለዋል።

በኢንስቲትዩቱ የህግ ስልጠናና ማማከር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ታረቀኝ ታፈሰ በክልላችን ወደ ውጭ ሀገር በህገ ወጥ መንገድ ከሚደረገው ጉዞ ባሻገር በአገር ውስጥ ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረገው ፍልሰት በሴቶችና ህጻናት ላይ ከፍተኛ እንግልትና ጉልበት ብዝበዛ እንዲሁም ጾታዊ ጥቃት እየተፈጸመ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ፋንታዬ ባስተላለፉት መልዕክት የስልጠናው ተሳታፊዎች ወንጀሉን በሚፈጽሙና በሚያመቻቹ አካላት ላይ በቂ ምርመራ በማድረግ አጣርቶ ለህግ በማቅረብና  ተመጣጣኝና አስተማሪ ቅጣት እንዲያገኙ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ስልጠናው ለሶስት ተከታታይ ቀናት እንደሚቀጥል ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን