የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ተደራጅተው በመስራት ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የጋራ የልማት ስራዎችን ማከናወን አለባቸው – አቶ ተስፋዬ ይገዙ

ሀዋሳ፡ ጥር 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ተደራጅተው በመስራት ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የጋራ የልማት ስራዎችን ማከናወን እንደአለባቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር እና የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ ገለጹ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምስረታ ጉባዔ በወላይታ ሶዶ ተካሄደ።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር እና ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ እንደተናገሩት ክልሉ ሰፊ ጸጋ ያለበት በመሆኑ ይህን ጸጋ ለህዝብ ልማት ለማዋል በጋራ ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል።

ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ተደራጅተው በመስራት ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎችን ማከናወን እንዲቻል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት እንዲቋቋም መደረጉን አንስተዋል።

ችግሮችን በውይይት የመፍታት አንድ ላይ አቅዶ መስራትን ባህል በማድረግ የፖለቲካ ምህዳርን በማስፋት ከፖለቲካ ፖርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት የክልሉ መንግስት ዝግጁ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ብዝሃነትን በአግባቡበ በማስተናገድ የሁሉም መብቶች እኩል ሊከበሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገር ልማት ያላቸው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ በውይይትና በሀሳብ የበላይነት የሚያምን ትውልድን መፍጠር ያስፈልጋል ነዉ ያሉት።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ በበኩላቸው ባላፉት ጊዜያት በሀገራችን የካበተ የዲሞክራሲ ግንባታ ባህል አናሳ መሆኑን ገልጸው ይህን ለመቅረፍና አሳታፊና አካታች የሆነ የፖለቲካ ስርዓትን ለመፍጠር ብልጽግና ፓርቲ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሀሳብ የበላይነትን በማመን ችግሮችን ተወያይቶ የመፍታት ባህልን በማሳደግ ህዝቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ ከሁሉም ፖለቲካ ፖርቲዎች ይጠበቃል ያሉት አቶ አለማየሁ፤ የፖለቲካ ፖርቲዎች በሰለጠነ መንግድ ችግሮችን ተወያይቶ የመፍታት ባህል ማሳደግ አለባቸው ነው ያሉት።

የሀገራዊ ፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ም/ቤት ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን በመገንባት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የጎላ ፋይዳ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው የተቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲ የጋራ ም/ቤት ይህን ዕውን እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ በትኩረት እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡

በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር እና ስራ ዕድል ፈጠራና የኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃለፊ አለማየሁ ባውዲ፣ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ም/ቤት ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ እና የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ተገኝተዋል።

ምንጭ፡ የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን