የኢትዮጵያን የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲናነት ለማፅናት ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅዖ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ጥር 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢትዮጵያን የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲናነት ለማፅናት ሁሉም የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዶክተር መለስ ዓለም ዛሬ (ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም) ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የዲፕሎማሲ ሳምንት የኢትዮጵያን የደለበ የዲፕሎማሲ ታሪክ እና ወረት ለዜጎች እና ለዲፕሎማቲክ ማኀበረሰብ በማስገንዘብ ረገድ የጎላ ሚና መጫወቱን ገልፀዋል።
ከጥር 02 እስከ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የጊዜ ገደብ የተያዘለት የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ እስከ 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ድረስ መራዘሙንም ቃል አቀባዩ ለጋዜጠኞች ገልፀዋል።አዲስ አበባ መቀመጫቸውን ያደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኀበረሰቦች አውደ ርዕዩ በተገቢው ሁኔታ በቂ ጊዜ ተሰጥቶት መታየት እንዳለበት አስተያየት መስጠታቸውን ቃል አቀባዩ አብራርተዋል።
የአውደ ርዕዩ መራዘም በተለይ ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ዋና መሠረት እንደመሆኗ በቀጣይ በሚካሄደው 37ኛው የመሪዎች ጉባዔ የሚሳተፉ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን አውደ ርዕዩን እንዲመለከቱ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ይኸ ውሳኔ አዲስ አበባን የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲናነት የማፅናት የተግባር እንቅስቃሴ አንዱ አካል ነው። በዲፕሎማሲ ሳምንቱ አፍሪካውያን ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ዋና ምሠሶ መሆኗን በቃል ብቻ ሳይሆን ያከናወነቻቸውን የተግባር ሥራዎች በአይናቸው እንዲመለከቱ ዕድል ይፈጥራል።
በቀጣይም “እያንዳንዱ ዜጋ የአገሩ ዲፕሎማት ነው” የሚለውን አስተሳሰብ በስፋት ወደ ተግባር ለመለወጥ አውደ ርዕዩ አንድ ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ቃል አቀባይ አስረድተዋል። ቃል አቀባዩ 44ኛው የሥራ አስፈጻሚዎች መደበኛ ስብሰባ እንደ አውሮፓውን አቆጣጠር የካቲት 6 እና 7 ቀን 2016ዓ.ም እና 37ኛው የመሪዎች ጉባዔ ደግሞ የካቲት 6 እና 10 ቀን 2024 በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ገልፀዋል።
ቀዳሚው እንደ ሕብረቱ መቀመጫ እና የጉባዔው አስተናጋጅ አገር በሁሉም ዘርፍ ጉባዔው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጋለች።በብሔራዊ ደረጃ የጉባዔው ዝግጅት ኮሚቴው ከአፍሪካ ሕብረት የፕሮቶኮል ክፍል ጋር በመተባበር ለጉባዔው አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉም በአምባሳደር ዶክተር መለስ ተብራርቷል።
የኢትዮጵያ ዝግጅት ጉባዔውን ማስተናገድ ብቻ ሳይሆን የራሷን ብሔራዊ ጥቅም በጉባዔው እንዲጎላ ለማድረግም መዘጋጀቷንም ገልፀዋል። ከግብርና፣ ከአረንጎዴ ዓሻራ እና ከቱሪዝም ዘርፍ አንጻር የተሠሩ ሥራዎችን ለማስተዋወቅ ዕድል የሚፈጥር ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ከጉባዔው ጎን ለጎን በሚካሄዱ የጎንዮሽ የሁለትዮሽ ስብሰባዎች ብሔራዊ ጥቅሞቿን በሚያስጠብቁ አጀንዳዎች ላይ ተዘጋጅታለች ብለዋል።
አምባሳደር መለስ(ዶ/ር)በአንድ ጊዜ በአንድ ቦታ የሚደረገው የኮንፍራንስ ዲፕሎማሲ በገንዘብ ቢተመን እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።50 የሁለትዮሽ ውይይት ለማድረግ ወደ 50 አገራት መጓዝ ይጠይቃል፡፡ይኸ ደግሞ ወጪው ከባድ ነው።አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ መሆኗ አንዱ እና ትልቁ ጠቀሜታ ይህን መሠል ዕድል ማመቻቸቱ ነው ብለዋል።
የኢትዮ-ሩስያ የፖለቲካ ምክክር እና የቢዝነስ ፎረም በሞስኮ ከነገ ጀምሮ እንደሚካሄድ አምባሳደር ዶክተር መለስ ገልፀዋል።
ቃል አቀባዩ በሳምንቱ ኢትዮጵያ ያካሄደቻቸውን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተም ለጋዜጠኞች ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ እና ማብራሪያ መስጠታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ