በልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ህብረተሰቡን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ለአካባቢውና ለሀገሩ ሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር አስገነዘበ

በልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ህብረተሰቡን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ለአካባቢውና ለሀገሩ ሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር አስገነዘበ

ሀዋሳ፡ ጥር 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ህብረተሰቡን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ለአካባቢውና ለሀገሩ ሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር አስገነዘበ።

የልዩ ወረዳው ምክር ቤት 4ኛ ዙር 30ኛ መደበኛ ጉባኤውን በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ፈቱዲን ሙዘሚል በዚህ ወቅት እንደገለፁት በየደረጃው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በሪፖርት ከመገምገም ባለፈ እስከ ታችኛው መዋቅር በመውረድ በትክክል መኖራቸውን የማረጋገጥ ሥራ እየተሰራ ነው።

በበጀት አመቱ ባለፉት 6 ወራት የተለዩ ጠንካራ ጎኖችና ውስንነቶችን በመለየት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መረባረብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኑ ሻቡዲን ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀሞ ሪፖርት በልዩ ወረዳው በበጀት አመቱ ግማሽ አመት ለማከናወን በተያዙ ዋና ዋና ግቦች አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል::

የአርሶ አደሩን ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰራው ስራ በ2015/16 የምርት ዘመን በበልግና በመኸር እርሻ ከ16ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መልማቱንና በዚህም ከ1 ሚሊዮን 2መቶ ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ባቀረቡት ሪፖርት ገልፀዋል።

በቀጣይ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት እንዳይገጥም ከወዲሁ የቅድመ ዝግጀት ስራ በመስራት ማዳበሪያ ወደ ልዩ ወረዳዉ ማዕከል የማስገባት ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል::

በትምህርት ዘርፍ የመማሪያ መጽሐፍት አጥረት ለመቅረፍና የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

የወባ በሽታን ለመካላከል፣ ማህበረሰቡን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሁም የወረዳው ገቢ ለማሳደግና ሌሎችም በልዩ ወረዳው የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም ነው አቶ ዘይኑ ያመላከቱት።

በልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ህብረተሰቡን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ሰላም ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም ሁሉም ለአካባቢውና ለሀገሩ ሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የጉባኤው ተሳታፊ የምክር ቤት አባላት በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በመንገድ መሰረተ ልማት ጥራት ጉድለትና በሌሎችም ጉዳዮች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን አንስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

በተለይም የሚሰሩ ስራዎች ጥራትና ደረጃ በማሻሻልና ወቅቱን የሚመጥኑ እንዲሆኑ ለማስቻል በትኩረት መስራት እንደሚገባ በጉባዔው ተገልጿል።

ምክር ቤቱ በዉሎው የልዩ ወረዳውን የ2016 በጀት መርምሮ ያፀደቀ ሲሆን በተጎደለ የካቢኔ አባል ምትክ የቀረበለትን ሹመት መርምሮ በማፅደቅ ተጠናቋል።

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን