ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በሲዳማ ክልል የበጋ መስኖ ልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የበጋ መስኖ ልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው።

በመስክ ምልከታው ላይ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ፣ በብልፅግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሀም ማርሻሎ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም ተገኝተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝታቸው በሸበዲኖ ወረዳ በአርሶ አደሮች እና በማህበር በተደራጁ ወጣቶች በበጋ መስኖ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።

የሸበዲኖ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኤልያስ አየለ በወረዳው በዘንድሮ የበጋ መስኖ ሥራ 2ሺህ 885 ሄክታር መሬት በቲማቲም፣ በጥቅል ጎመን፣ በሽንኩርትና በተለያዩ ሰብሎች እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቶችን በግብርና ልማት ሥራ ላይ በስፋት ለማሰማራት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በመስኖ ሥራ ብቻ 135 ወጣቶችን በማሳተፍ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የክልሉ አመራሮች ከሸበዲኖ ወረዳ በተጨማሪ በሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ እና ሌሎች አካባቢዎች ያሉ የመስኖ ልማት ሥራዎችንም ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።(ኢዜአ)