በተጨብረበረ የባንክ ስቴትመንት የኢንቨስትመንት መሬት ለመረከብ ስንቀሳቀስ የነበረ ግለሰብ በህግ ቁጥጥር ስር ዋለ

በአሪ ዞን በቅባት እህል ዘርፍ የኢንቨስትመንት መሬት ለመረከብ ዋልዕሸት ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በሚል ስያሜ የሚንቀሳቀሰው ማህበር ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ተጠርጣሪ አቶ ግዛው ነጋሽ ለኢንቨስትመንት የሚያስፈልገውን ካፒታል 30 በመቶ ማለትም 32 ሚሊዮን 246 ሺህ 340 ብር እንዲሁም ከባንክ ብድር 70 በመቶ ማለትም 75 ሚሊዮን 246 ሺህ 460 ብር በጠቅላላ 107 ሚሊዮን 492 ሺህ 800 ካፒታል ማሟላት ይጠበቅበታል ።

በቀድሞ የደቡብ ኦሞ ዞን ካቢኔ ማህበሩ የጠየቀው 10 ሺህ ሄክታር ቢሆንም ባቀረበው ካፒታል 400 ሄክታር እንዲሰጣቸው ውሳኔ ተላልፎ ለቀድሞ የደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ጭምር መረጃው እንዲደርስ መደረጉን የአሪ ዞን ኢንቨስትመንት መምሪያ ሀላፊ አቶ ፍቅረስላሴ ጀማል በሰጡት መግለጫ አስታውሰዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ግለሰቡ በወቅቱ የሚጠበቅበትን አሟልቶ ሳይረከብ ዘግይቶ በአሁን ወቅት መሬቱ ወደ ልማት መግባት እንዳለበት አዲሱ የአሪ ዞን ኢንቨስትመንት መምሪያ ውሳኔ መተላለፉን የመመሪያው ሀላፊ ገልፀዋል።

ተጠርጣሪው ግለሰብ መሬቱን ለመረከብ ሲል ከአዲስአበባ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጎፋ ካምፕ ቅርንጫፍ የድርሻውን 30 በመቶውን ቆጥብያለሁ በሚል 48 ሚሊዮን 650 ሺህ ብር የባንክ ስቴትመንት ለአሪ ዞን ኢንቨስትመንት መምሪያ ያቀርባል።

ዋልዕሸት ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ ያቀረበውን የባንክ ስቴትመንት ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ መምሪያው በአቅራቢያ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ህጋዊ ደብዳቤ ይፅፋል።

ንግድ ባንኩም ይህንን መነሻ በማድረግ ሲያጣራ በግለሰቡ አካውንት የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን አለመኖሩን ያረጋግጣል።

በዚህም ተጠርጣሪ ግለሰብ የባንክ ስቴትመንት አመጣሁ ወዳለው አዲስአበባ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መረጃው እንዲደርስ ስደረግ ባንኩም በግለሰቡ የተከፈተ አካውንት መኖሩንና በአካውንቱ ገንዘብ አለመኖሩን ዳግም ያረጋግጣል ።

በዚህ ብቻ ሳያበቃ ግለሰቡ ከአዲስአበባ ከተጠቀሰው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጎፋ ካምፕ ስቴትመንት ተሰቶኛል ብሎ ያቀረበው ከባንኩ ያልተሰጠ ከመሆኑም ባለፈ ሐሰተኛ ሰነድ መሆኑም ጭምር ይረጋገጣል።

ይህንን ጉዳይ በጥንቃቄ ሲያጣራ የነበረው የአሪ ዞን ኢንቨስትመንት መምሪያ መረጃዎችን አደራጅቶ ለአሪ ዞን አስተዳደርና ፖሊስ መምሪያ ያሳውቃል።

ግለሰቡ ጉዳዩን ለማስፈፀም የአሪ ዞን ኢንቨስትመንት መምሪያ በተገኘበት በፀጥታ አካላት በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉን የመምሪያው ሀላፊ አቶ ፍቅረስላሴ ጀማል ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ጂንካ ቅርንጫፍ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳር ጉዳዩን በመደገፍ ላበረከተው አስተዋፅኦ አቶ ፍቅረስላሴ በመምሪያው ስም አመስግኗል።

ሀላፊነት በጎደላቸው አካላት በሚደረግ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ በርካታ የሀገር ሀብት ሳይለማ ከመቅረቱ ባሻገር ብልሹ አሠራር በሀገሪቱ እንዲንሰራፋ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ ሁሉም አካል ጉዳዩን ልያወግዝ ይገባል ሲል መልዕክት አስተላልፏል ።

በአካባቢው በተለያዩ ዘርፎች የኢንቨስትመንት መሬት ተረክበው ምንም ሳያለሙ እስከ 25 ዓመታት የቆዩ ባለሀብቶች መኖራቸውን የገለፁት አቶ ፍቅረስላሴ ፈጥነው ወደ ተግባር መግባት እንዳለባቸው አሳስበው ይህ ሳይሆን ቢቀር መመሪያን የተከተለ እርምጃ እንደሚወሰድ አመላክተዋል።

የአሪ ዞን ፖሊስ መምሪያ የማህብረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዲቪዥን ሀላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ሽብሩ አማሬ እንደገለፁት ተጠርጣሪ ግለሰቡ በአሁን ወቅት በህግ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የማጣራቱ ሂደት ሲጠናቀቅ ክስ እንዲመሠረት ይደረጋል ብለዋል።

በዞኑ ኢንቨስትመንት መምሪያ በኩል የተደረገው ተግባር የሚደነቅ ነው ሲሉም ምክትል ኢንስፔክተር ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን