የሶያማ ከተማ አስተዳደር ግብር ከፋዮች ወቅቱን ያላገናዘበ ግብር ለመክፈል ተገደናል አሉ

የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ ለ6 ዓመታት ሳይሻሻል የቆየ የደረጃ ማሻሻያ ተደርጎ እንጂ ያለ አግባብ የተወሰነ አለመሆኑን ገልጿል።

አቶ ሀሺም ብማ እና ዘነበ ዳለታ የደረጃ “ሐ “ግብር ከፋይ ናቸው። በተለይ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ከቀድሞ በተለየ መልኩ የግብር ትመናው ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ጠቅሰው በነበረው የድርቅ እና ሌሎች ተጓዳኝ ምክናቶች ተቀዛቅዞ የነበረው ኢኮኖሚ እንደ ዋነኛ ምክንያት አንስተዋል።

ቅሬታ አስገብተው ምንም ዓይነት ምላሽ ሳይሰጣቸው ለመክፈል መገደዳቸውን በማስረዳት አቶ ሀሽም ከነጋዴው ማህበረሰብ የተወከሉ የገቢ ግብር ተማኝ ኮሚቴ አባልም ጭምር ስለ ነበሩ ቅሬታውን ለማየት እድሉ እንደነበራቸው ተናግረዋል።

የሶያማ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከድር መሐመድ ከበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ ለግብር ከፋዮች የግንዛቤ ማስጨበጫ እየሰጡ የቆዩ እንደ ነበር አንስተው ደረጃ “ሐ” 7 መቶ 16 ደረጀ “ሀ” 22 እና ደረጃ “ለ” 12 ግብር ከፋዮች ጋር እየሠሩ መቆየታቸውን አብራርተዋል።

በመሆኑም ባለፉት 6 ዓመታት በግብር ከፋዮች የደረጃ ለውጥ ሳይደረግ የቆየ ስለነበር የደረጃ ለውጥ ለማድረግ እና ለማሻሻል የነጋዴ ተወካይ ጨምሮ ግብረ ኃይል አቋቁሞ በማጥናት የደረጃ ለውጥ ለማድረግ መወሰኑንም አስረድተዋል።

በተለይም የደረጃ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ መጠነኛ ጭማሪ በመታየቱ ቅሬታ ያቀረቡ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ቢኖሩም ሂደቱን ጠብቆ የተሠራ በመሆኑ እና ሳይሻሻልም ረጅም ጊዜ የቆዬ በመሆኑ የቀረበው ቅሬታ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

ዘጋቢ፡ አብዶ አያላ- ከይርጋጨፌ ጣቢያችን