የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የልማት ስፓሻል ፕላን ዝግጅት የግንዛቤ ማስጨበጫና ማስቀጠያ መድረክ መካሄድ ጀመረ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የልማት ስፓሻል ፕላን ዝግጅት የግንዛቤ ማስጨበጫና ማስቀጠያ መድረክ መካሄድ ጀመረ

ሀዋሳ፡ ጥር 21/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የ30 ዓመታት የእድገትና የልማት አመልካቾችን መለየት የሚያስችል የልማት ስፓሻል ፕላን ዝግጅት ለክልሉ ስትሪንግ ኮሚቴና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የዕለቱ የክብር እንግዳ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንደሻው ጣሰው፥ በክልሉ በሚካሄደው የስፓሻል ፕላን ዝግጅት ላይ የሚሰበሰበው መረጃ ጥራት ያለው እንዲሆን ለማድረግ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

የሚሰበሰበው መረጃ ለሚዘጋጀው የልማትና የእድገት አመልካች ፍኖተ ካርታ ግብአት ሆኖ እንዲያገለግል በየደረጃው ያላችሁ አካላት ተገቢውን ድጋፍና ትብብር በማድረግ ስራውን ስኬታማ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የዚህ የልማት ስፓሻል ፕላን ዝግጅት ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የከተሞችን እድገት ለማረጋገጥ፣ የመሬት አጠቃቀምን ለማሻሻል እና ከተማና ገጠርን ለማስተሳሰር ጥናቱ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል በበኩላቸው የክልሉን የራዕይ ቀረጻ፣ የመሬት አጠቃቀም ፕላን ንደፈ ሀሳብ ዝግጅት እና የትግበራ ስትራቴጂ ዝግጅት ያልተከናወኑ ቀሪ ተግባራት በመሆናቸው በተያዘው በጀት አመት ለማጠናቀቅ የየድርሻችንን ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

አጠቃላይ በክልሉ የልማት ስፓሻል ፕላን ዝግጅት ሊኖር የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሁሉ አቀፍ ጠቀሜታ አንጻር ዝርዝር መረጃ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱን ጨምሮ የክልሉ ካቢኔ አባላት፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳ አስተዳዳሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተግኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ