የማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት በልዩ ትኩረት ሊፈጸሙ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አሳሰበ

የማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት በልዩ ትኩረት ሊፈጸሙ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አሳሰበ

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ፥ በክልሉ የተጀመረውን ማህበራዊ ፍትህ የማረጋገጥ ተግባር በትምህርትና በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን የተቀመጡ ግቦች ሊሳኩ በሚችሉበት አግባብ መፈጸም እንደሚገባ አሳስበዋል።

በክልሉ የሚገኙ የዞንና ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪዎችና ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን እና በትምህርት ልማት ዘርፍ የመማሪያ መጽሐፍት አሰባሰብ እቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ተወያይተዋል።

በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን እና በትምህርት ልማት ዘርፍ የመማሪያ መጽሐፍት አሰባሰብ፥ ቀደም ሲል በእቅድ ከተያዘው አንጻር ተግባራት ያሉበትን ደረጃ በዝርዝር ፈትሾ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት የቀጣይ አቅጣጫ በሪፖርቱ ቀርቧል።

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ከክልሉ ሁሉም አከባቢዎች የተገኙት የዞንና የልዩ ወረዳ አስተዳዳሪዎችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በቀረበው ሪፖርት ላይ ሃሳብና አስተያየታቸውን አቅርበዋል።

ከማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን እና ከትምህርት መጽሐፍ አሰባሰብ አንጻር በሪፖርቱ የቀረበው ጠንካራና ደካማ አፈጻጸም በፍጥነት ለማሻሻል እንደሚሰራና የአመራር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። በተለይ ከዞንና ልዩ ወረዳም በተመሳሳይ ጉራማይሌ በሆነ አፈጻጸም ደረጃ የሚገኙ መዋቅሮች ወጥነት ባለው መልኩ ባልተንጠባጠበ ተግባር ማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ንጉሴ አስረስ በበኩላቸው በቀረበው የአፈፃፀም ልዩነት ዙሪያ ምንም ማስተባበያ መስጠት ሳያስፈልግ አመራሩ የቀሩ ተግባራትን ለማሳካት መጣር እንዳለበት ጠቁመዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በዚህ ወቅት በሰጡት መመሪያ ሁሉም አስፈፃሚ የማህበራዊ ፍትህ እንዲረጋገጥ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተግባራትን ቆጥሮ መፈጸም እንዳለበት አሳስበዋል።

የአፈፃፀም ወጥነት መጓደል፣ የተሰበሰበ ገንዘብ ወደ ባንክ ገቢ አለመሆንና ሌሎች ችግሮችንም ፈጥኖ ማረም እንደሚገባ ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ