ከ35 ሺህ በላይ ነባርና አዳዲስ አባላትን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ከ35 ሺህ በላይ ነባርና አዳዲስ አባላትን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ከ35 ሺህ በላይ ነባርና አዳዲስ አባላትን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የኮሬ ዞን ጤና ዩኒት ገለጸ።

የኮሬ ዞን ጤና ዩኒት ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ተቋም አስተባባሪ አቶ ዘርሁን በሪሶ እንደተናገሩት፤ ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን በዞኑ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አንድ ዓመት የደረሰ ሲሆን ለውጦች ተመዝግበዋል።

በዞኑ 24 ሺህ 4 መቶ 64 ከፋይና መክፈል የማይችሉ አባላትን ይዞ የተጀመረው አገልግሎቱ፣ ውል በገቡበት ጤና ተቋማት አባላቱ በመገልገል ላይ ናቸው ብለዋል።

በ2016 ዓ.ም የንቅናቄ መድረክ ተደርጎ የነባር አባላት እድሳትና አዳዲስ አባላትን የማፍራት ሥራ ተጀምሮ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ዘሪሁን፣ 35 ሺህ በላይ ነባርና አዳዲስ አባላትን ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዟል ነው ያሉት።

ከዚህም 17 ሚሊየን 5 መቶ ሺህ ብር ለአገልግሎቱ ይሰበሰባልም ብለዋል።

ከተያዘው ጊዜ አንጻር የእቅድ አፈጻጸሙ አዝጋሚ መሆኑንና በጥር ወር መግቢያ ከተደረገው ንቅናቄ መነሻ፣ በመረጃ መለዋወጡ በኩል ያለው ክፍተት እንዳለ ሆኖ፣ መክፈል የማይችሉትን ሳይጨምር 5 በመቶ ብቻ አዳዲስ አባላትን ማፍራት ስለመቻሉ ተናግረዋል።

አቶ ዘርሁን እንደገለጹት፣ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አባላት፣ የመታወቂያው ባለቤት ለመሆን የቤተሰቦቻቸውን ዝርዝርና ፎቶ በማቅረቡ በኩል ያላቸውን ክፍተት ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል።

የመረጃ ልውውጥ ክፍተቶችን ለመሙላት ባለድርሻ አካላትም በተገቢው ጊዜ በወቅቱ እንዲያደርሱም ነው ያሳሰቡት።

የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ቤተሰቦቹን ለማሳከም በኬሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ያገኘናቸው አቶ ታከለ ኮሌጅ፣ የማአጤመ አገልግሎት መጀመሩ ቤተሰቦቹን ከወጭ እንደታደጋቸው ገልጸዋል።

ሌላኛው ተገልጋይ አቶ ወንድማገኝ ሳድሳ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ፋይዳው የጎላ በመሆኑ የመድን ዋስትና መታወቂያቸውን ቀድመው ማሳደሳቸውን አብራርተዋል።

ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን