ባህል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከርና ታሪካዊ ዕሴቶችን በማጎልበት በኩል ሚናው የጎላ በመሆኑ ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ጥር 19/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ባህል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከርና ታሪካዊ ዕሴቶችን በማጎልበት በኩል ሚናው የጎላ በመሆኑ ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ ተገለፀ።
የሸኮ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ቲካሻ ቤንጊ” በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል።
ከጥር 17 እስከ 19 ዓ.ም እየተከበረ የሚገኘው የሸኮ ብሔረሰብ ባህላዊ የዘመን መለወጫ “ቲካሻ ቤንጊ” በዓል በወንድም ብሔረሰብ በቤንች፣ ካፋ፣ ሸካ፣ ዲዚ፣ ማዣንግ እንዲሁም በሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ ጭፈራ በድምቀት እየተከበረ ነው።
የሸኮ ብሔረሰብ እንግዳ ተቀባይ የሰውን ሀቅ የማይፈልግ ለሌላው ተምሳሌት የሚሆን ባህል ያለው እና ከ50 ዓመት በኃላ ባህላዊ የዘመን መለወጫ በዓሉን እያከበረ የሚገኝ ብሔረሰብ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩረታ ተናገረዋል።
ባለፉት ጊዜያት ዜጎች ተሰብስበው ደስታቸውን የሚገልፁበት ወቅቶች እንዳልነበር የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ ገልፀው በተለይም ሸኮ ከነበረበት ችግር ወጥተው ስለልማትና ባህል ትኩረት መስጠቱ የምሁራኑ ሚና የጎላ ቢሆንም መንግስትም በቀጣይ አብሮ ይሰራል ብለዋል።
ባህል የአንድ ብሔረሰብ ማንነት መገለጫ መሠረት በመሆኑ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማስተሳሰር ረገድ የማይተካ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ ተናገረዋል።
የብሔረሰቡ ቱባ ባህልም ታሪካዊ ዕሴት ተጠብቆ እንዲቆይ መጪው ትውልድና ምሁራኑ በአባቶች ስር ቁጭ ብሎ በታሪኮች ላይ ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ ፋንታሁን አስገንዘበዋል።
በብሔረሰቡ ዘንድ የሚገኘውን ዕምቅ ባህል እንዲታወቅና በዩኒስኮ እንዲመዘገብ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን ተናገረው የሸኮ ብሔረሰብ ለዘመናት የተፈጥሮ ሀብትን ጠብቆ ያቆየው ተሞክሮ የሚቀመረበት በዓል ነው ብለዋል።
የሸኮ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ቲካሻ ቤንጊ” በዓል ክረምት አልፎ በጋ ሲተካና ምርት ሲሰበሰብ የሚከበር እንደሆነ የሸኮ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ አሪ ጉረሙ አውስተው ለበዓሉ የበኩላቸውን የተወጡትን አካላት አመስገነዋል።
በበዓሉ የተገኙ ተሳታፊዎችም ለዘመናት በህብረተሰቡ ዘንድ የቆየው የብሔረሰቡ ባህል ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ መደረጉ እንዳስደሰታቸውና አንዱ ብሔረሰብ ከሌላው ጋር ያለው ሰላማዊ ግንኑኝት እንዲጠናከር ያስችላል ብለዋል።
በዓሉን የሸኮ ብሔረሰብ ጎሳ መሪ ኮምቱ በዲ የመረቁ ሲሆን የሸኮ ብሔረሰብ አባት የሆነው ጀባ ቡረጂ እንዲሁም የካፋ ንጉስ ቀጣዩ አመት አከባቢው የሰላምና የአብሮነትና አንድነት ባህል የሚጠናከረበት ዘመን እንዲሆን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ
ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመምራት እና በመጠቀም የአካባቢን ገጽታ መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ
የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል ተገለጸ