የሸኮ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ቲከሻ ቤንጊ” በዓልን በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጀት ተጠናቋል – የወረዳው ዋና አስተዳደር

የሸኮ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ቲከሻ ቤንጊ” በዓልን በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጀት ተጠናቋል – የወረዳው ዋና አስተዳደር

ሀዋሳ፡ ጥር 16/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሸኮ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ቲከሻ ቤንጊ” በዓልን በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጀት ማጠናቀቁን የወረዳው ዋና አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የብሔረሰቡ የዘመን መለወጫ ቲከሻ ቤንጊ በዓል ከጥር 17 እስከ 19/2016 ዓ.ም እንደሚከበርም ተገልጿል።

የሸኮ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ አሪ ጉረሙ ለጣቢያችን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለፁት በወረዳው በድምቀት የሚከበረው የዘመን መለወጫ “ቲከሻ ቤንጊ” በዓል የብሔረሰቡ አባላት በዓመት ያመረቱት ምርቶች በፈጣሪ ተጠብቆ መድረሱን የሚገልፅ የምስጋናና የደስታ ፕሮግራም እንደሆነም ተናግረዋል።

በዓሉ በቀድሞ በደርግ መንግስት ይከበረ የነበረና ከዛ በኋላ ትኩረት ያልተሰጠው ሲሆን በአሁን ሰዓት በብልፅግና መንግስት ብሔረሰቡን ለማስተዋወቅ በአደባባይ ላይ ገኖ የወጣ መሆኑን የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው በዓሉ ለህብርተሰቡ ከፍተኛ ልማት ሰላምና ዕድገትን የሚያስተምር እንደሆነም አብራርተዋል።

በወረዳው ማዕከል ከጥር 17 እስከ 19/2016 ዓ.ም የሚከወነው የሸኮ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ቲከሻ ቤንጊ” በዓልን በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የገለፁት አቶ አሪ በበዓሉ የአከባቢው ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች፣ አጎራባች ወረዳና ዞኖች እንዲሁም የክልልና የፌደራል የክብር እንግዶች እንደሚገኙና የፓናል ውይይትም እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

ለበዓሉ ከፀጥታ ኃይሉ ባሻገር ከ50 በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን አሰልጥነው ማዘጋጀታቸውንና በዓሉ በብሔረሰቡ ጎሳ መሪ ምርቃት ተጠቃልሎ በማግስቱ መላው የህብረተሰቡ አባላት ወደየልማታቸው መመለስ እንዳለባቸውም አቶ አሪ አንስተዋል፡፡

እንግዳ ተቀባዮቹ የከተማው ነዋሪዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ማደረግ እንዳለባቸውም የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አስገንዘበዋል።

በክበረ በዓሉ የሚታደሙ የጎሳ መሪዎች በባህላዊ ጭፈራ እንደሚገቡና የሸኮ ብሔረሰብ ተወላጆችና የአከባቢው ነዋሪዎች በዕለቱ ባህሉን የሚገልፅ አልባሳትና ጭፈራዎችን ይዘው መቅረብ እንዳለባቸው አቶ አሪ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን