በወላይታ ዞን ዳሞት ወይዴ ወረዳ የበዴሣ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የወላድ እናቶችና የጨቅላ ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገለፀ
ሀዋሳ፡ ጥር 14/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በወላይታ ዞን ዳሞት ወይዴ ወረዳ የበዴሣ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የወላድ እናቶችና የጨቅላ ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ሆስፒታሉ በዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች የተካነ መሆኑ የተገልጋይ ዕርካታን ያሳደገ ስለመሆኑም ተመላክቷል፡፡
ከአጎራባች ወረዳዎች የሚመጡ ታካሚዎች ጭምር ተገቢውን አገልግሎት አግኝተው እንደሚመለሱ ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በበዴሣ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሳምሶን ሚልክያስ እንደተናገሩት፣ ምንም እንኳን ሆስፒታሉ በቅርብ ጊዜ የተቋቋመ ቢሆንም በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ ነባር የሕክምና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያልተናነሱ የተለያዩ የሕክምና አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።
መለስተኛ ቀዶ ሕክምናን ጨምሮ በርካታ የሕክምና አገልግሎቶችም በበዴሣ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እየተሰጡ እንደሚገኙ አቶ ሳምሶን ገልፃዋል።
የነገ አገር ተረካቢ ዜጎችን ከማፍራት አኳያ የጨቅላ ሕፃናትን ሞት መቀነስ እንዲሁም እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንስቶ መጠነ-ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ በሆስፒታሉ የሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ብሩክ ኢያሱ ተናገረዋል።
የእናቶችና የሕፃናት ሕክምና ክፍል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ክፍሌ ለማ እንደገለጹት፣ ለእናቶችና ሕፃናት የሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት የእናቶችና ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ የታቀደ ነው።
በዚህም በተለያዩ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች የታገዘ አገልገሎት ስለሚሰጥ በርካታ ተገልጋዮች ወደ ሆስፒታሉ ይመጣሉ።
በሆስፒታሉ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ከመጡ ወላድ እናቶች መካከል ወይዘሮ መቅደስ አልታዬ እና ወይዘሮ መሠረት ኤልያስ በተደረገላቸው የሕክምና ዕርዳታ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ሌሎች እናቶችም በጤና ተቋማት የመውለድ ልምድ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም እናቶቹ በጋራ በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ : ፍቃዱ ማቴዎስ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ