በጎፋ ዞን ከ38ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተፋሰስ እንደሚለማ የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ
ሀዋሳ፡ ጥር 14/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) “የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችንን በማሳደግ ግብርናን እናዘምናለን “በሚል መሪ ቃል የተፋሰስ ልማትና የበልግ አዝመራ ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ በዛላ ወረዳ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ፋንታዬ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የአፈር መሸርሸርን በመከላከል፣ የአየር ንብረት ለመጠበቅና ምርታማነትን ለመጨመር አስተዋጽኦ አበርክቷል።
የተፋሰስ ልማት ስራው በክረምት ወራት ለሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ልማት መሰረት የሚጥል በመሆኑ በዞኑ በሁሉም መዋቅሮች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማረም ምርታማነትን ማሳደግ የህልውና ጉዳይ ነው መሆኑን ነው አስተዳዳሪው የገለፁት።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ደግፈ በበኩላቸው በዞኑ በሁሉም አከባቢዎች በተዘጋጁ 175 ንዑስ በተዘጋጁ ከ38ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ፕሮግራም እንደሚለማ ገልጸዋል።
በየዓመቱ የሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ስራ ምርትና ምርታማነት በማሳደግና በረሃማነትን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እያበረከተ ነው ብለዋል።
በዘንድሮው የተፋሰስ ልማትም የአፈር ለምነትን የሚያስጠበቁ ስራዎች በማከናወን አሲዳማነትን የመከላከል ስራ በትኩረት እንደሚከናወን ገልጸዋል።
በያዝነው የበልግ ወቅት በሁሉም የሰብል አይነቶች 77ሺህ 518 ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን ከ4 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ስለመታቀዱ ነው ያብራሩት።
ከዚህ ውስጥ በአዝርዕት ሰብሎች ከ65ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር የሚሸፈን ሲሆን ምርታማነትን በሄክታር 24 ነጥብ 5 ኩንታል በማድረስ ከ1ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ስለመገኘቱ ነው ያስረዱት፡፡
የ2016 የተፋሰስ ልማት እና የበልግ እርሻ ዕቅድ በመምሪያው ምክትል ኃላፊዎች በአቶ ዕድገቱ እስራኤልና በአቶ ዮሐንስ በየነ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
የንቅናቄ መድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ለተፋሰስ ልማትና ለበልግ እርሻ ትኩረት በመስጠት የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
አርሶ አደር ማሄ ኩቴ እና አርሶአደር ዘሪሁን ኢዮብ በጋራ በሰጡት አስተያት እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም በተከናወነ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በአከባቢያቸው የተጎዱ መሬቶች በማገገም ላይ መሆናቸውን ጠቁመው በያዝነው ዓመትም ስራውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በበልግ እርሻም መሬታቸውን በአግባቡ አርሰውና አለስልሰው ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተሻለ ምርት ለማግኘት መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል።
በንቅናቄ መድረኩ፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ