እየተሰሩ ያሉ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ጥራትና ደረጃ ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ጥር 14/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የምክር ቤት ቋሚ ኮሜቴዎች ድጋፍና ክትትል በማጠናከር በየደረጃው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ጥራትና ደረጃ ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቀቤና ልዩ ወረዳ ምክር ቤት ጽ/ቤት ገልጿል።
የልዩ ወረዳው ምክር ቤት የሴቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ዘርፍ፣ የኢኮኖሚ ዘርፍ፣ የህግና ፍትህ መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴዎች በልዩ ወረዳው ባሉ ቀበሌያት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የመስክ ምልከታ አካሂደዋል።
በመስክ ምልከታው በበጀት አመቱ ላለፉት 6 ወራት በግብርና በትምህርት፣ በጤና፣ በህብረት ስራ ማህበራት፣ በቀበሌ ምክር ቤቶችና በሌሎችም ዘርፎች አየተሰሩ ያሉ ስራዎች የታዩ ሲሆን በተለይም በግብርናው ዘርፍ በመስኖ ልማት ስራ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታችና ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል።
በችግኝ ቅድመ ዝግጅት፣ በምርት አሰባሰብና በአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችና ያሉ ቀሪ ስራዎችን በጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል።
በትምህርት ዘርፍ በተለይም በቀቤና ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ከመምህራን አቅም ውስንነት፣ ከመማሪያ ክፍልና መፅሀፍት እጥረት፣ ከተማሪዎች የትምህርት ፍላጎት መቀዛቀዝና ውጤት ማሽቆልቆል፣ የላብራቶሪና አይሲቲ ክፍሎች የማስተማሪያ ግብዓቶች እጥረት ትኩረት የሚሹ ተግባራት መሆናቸውን ቋሚ ኮሚቴው አብራርቷል።
በጤናው ዘርፍ ከአምቡላንስ አጠቃቀም፣ ከመድሃኒት አቅርቦት ፣ በቀበሌያት የጤና ኤክስቴሽን ፕሮግራም ከማጠናከር የወባ በሽታ መጨመር እንዲሁም በወሸርቤ ጣጤሳ ጤና ጣቢያ ከባለሙያ እጥረትና ከግንባታ ጥራት መጎደል ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍ በቀጣይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ፈቱዲን ሙዘሚል በየደረጃው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በሪፖርት ከመገምገም ባለፈ እስከ ታቸኛው መዋቅር በመውረድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በትክክል መኖራቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በመስክ ምልከታው የተለዩ ጠንካራ ጎኖችና ውስንነቶችን በመለየት ግብረ መልስ ለፈፃሚና ለአስፈፃሚ ተቋማት ይቀርባል ያሉት አፈ ጉባኤው የሚስተዋሉ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በመቅረፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተለይም የሚሰሩ ስራዎች ጥራትና ደረጃ በማሻሻልና ወቅቱን የሚመጥኑ እንዲሆኑ በማስቻል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ ዋና አፈ ጉባኤው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ