ለትምህርት ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ  መስራት  እንደሚገባ ተገለፀ

ለትምህርት ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ  መስራት  እንደሚገባ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ጥር 13/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) አለም በቴክኖሎጂ አሁን ለደረሰበት ደረጃ  ዋናዉ ነገር ትምህርት በመሆኑ ለትምህርት ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ  መስራት  እንደሚገባ የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ ገልፀዋል።

በዞኑ አንሌሞ ወረዳ  በጭንጎ ልማት ማህበር ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የጭንጎ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤትን መልሶ ለመገንባትና ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተጥሏል።

የጭንጎ  ልማት ማህበር ሰብሳቢ ሀጂ ዘይኑ  ከድር እንደተናገሩት፤ ማህበሩ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን መንግስት እያደረገ ያለዉን ጥረት በማገዝ  ለትምህርት ቤቶች የመማሪያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ሲያደረግ ቆይቷል።

በሀገር ውስጥና ከሀገር ወጪ ያሉ የአከባቢው ተወላጆችን በማስተባበር በአዲስ አበባ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም መካሄዱን የገለጹት ሰብሳቢዉ በዚህም ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል መገበቱን ጠቅሰዉ በትምህርት ቤቱ የ6 ብሎኮች ግንባታ በዘመናዊ ሁኔታ ለማስገንባት ማቀዳቸውንም ተናግረዋል።

የአንሌሞ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፀደቀ ግርማ በበኩላቸው ልማት ማህበሩ ከዚህ ቀደምም በቀበሌው የተለያዩ  የልማት ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመው የጭንጎ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤትን መልሶ ለመገንባትና አዲስ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በመገንባት የተማረ ትዉልድን ለመፍጠር ልማት ማህበሩ  እያደረገ ያለው አሰተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ቀበሌው ለረዥም ዘመናት ጥያቄ ሆኖ የቆየዉ የመብራት  ችግር መንግስት ባደረገዉ ብርቱ ጥረት ተቀርፎ  አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የገለጹት አቶ ፀደቀ ቀበሌው ሙሉ በሙሉ የመብራት ተጠቃሚ መሆኑንም ተናግረዋል። ይህም ለትምህርት  ስራ የራሱ አስተዋጽኦ ያለው ስለመሆኑ በመጠቆም።

የአካባቢው ማህበረሰብ  በቀጣይም  በሌሎች  ልማቶችም  ተሳትፎዉን እንዲያጠናክሩ  የዞኑ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ  እንዲያደርግም አቶ ፀደቀ  ጠይቀዋል።

የሀዲያ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ክበሞ ዴታሞ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በዞኑ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል 39 ትምህርት ቤቶች በደረጃ አንድ ያሉ በመሆናቸው ወደ ደረጃ 3 ለማሸጋገር ህብረተሰቡን ያሳተፉ ተግባራት መጀመራቸዉን ጠቅሰዉ የጭንጎ ልማት ማህበር በዘርፉ እያደረገ ያለው ተሳትፎ ለሌሎች ተሞክሮ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዞኑ በትምህርት ቤቶች የሚስተዋለዉን የመጽሐፍት እጥረትን ለማቃለል በሚያስችል መልኩ ከ230 ሚሊየን ብር በላይ ከህብረተሰቡ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዉ ይህም የተሳካ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ  በበኩላቸው አለም በቴክኖሎጂ አሁን ለደረሰበት ደረጃ  ዋናዉ ነገር ትምህርት በመሆኑ ለትምህርት ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ  መስራት  እንደሚገባ ተናግረዋል።

የህብረተሰቡን ኑሮ መቀየር የሚቻለው ተደጋግፎ መስራት ስቻል በመሆኑ ልማት ማህበሩ የአከባቢውን አንገብጋቢ የልማት ችግሮችን ለመቅረፍ እያደረገ ያለዉ ተግባር የሚያስመሰግን መሆኑንም ተናግረዋል።

የጭንጎ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤትን መልሶ ለመገንባትና አዲስ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ለመገንባት በተጀመረዉ ስራ ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ አካላትንም አቶ አብርሃም አመስግነዋል።

የመንግስትን እጅ ሳይጠብቅ የልማት ስራ እየሠራ  ለሚገኘው  ለጭንጎ አካባቢ  ማህበረሰብ የዞኑ መንግስት አስፈላጊውን  ድጋፍ  እንደሚያደርግም ዋና አስተዳዳሪው ገልፀዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡት የጭንጎ ቀበሌ ነዋሪዎች እንደገለፁት፤  መብራት ባለመኖሩ ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች  ሲዳረጉ መቆያታቸዉን አስተውሰዉ  አሁን ላይ የመብራት ችግር ሙሉ በሙሉ መቀረፉንና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በአካባቢው ተወላጅ ባለሀብቶች የልማት እንቅስቃሴ የጭንጎ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትን መልሶ ለመገንባት የመሠረተ ድንጋይ በመጣሉ እጅግ መደሰታቸውንና አቅም በፈቀደ ሁሉ ድጋፋቸውን አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ –  ከሆሳዕና ጣቢያችን