ክልሎቹ የጋራ ንብረት ጥበቃ ላይ ስምምነት አካሄዱ
ሀዋሳ: ጥር 12/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ የጋራ ንብረቶችን የሲዳማ ክልል የፀጥታ ሀይል ጥበቃ እንዲያደርግ የሚያስችል የመተማመኛ ሰነድ ላይ ስምምነት ተፈራርመዋል::
የስምምነት ፊርማ የተካሄደው ለቀድሞ የደቡብ ክልል የፖሊስ ሠራዊት አባላት የሽኝት መርሀግብር በተካሄደበት ወቅት ነው::
በዚሁ የሽኝት መርሀግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽመልስ ቶማስ ሠራዊቱ የቀድሞው የደቡብ ክልል ፖሊስ በኢትዮጵያዊ የአንድነት ስሜት ያገለገለ ነው ብለዋል::
ሠራዊቱ ለህዝብና ለሀገሩ ላሳየው ተቆርቋሪነት አራቱም ክልሎች ኩራት ይሰማናል ሲሉ ተናግረዋል::
የለውጡ መንግስት የህዝብን ጥያቄ የሚያደምጥና የሚመልስ ነው ያሉት ደግሞ በመርሀግብሩ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ ናቸው::
የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ በክልል ከተደራጀ በኋላ የተቀሩት ሶስት ክልሎች ተደራጅተው እስኪወጡ ድረስ የሲዳማ የፀጥታ ኃይል ለህዝብ ሠላምና ደህንነት የሚጠበቅበትን መወጣቱን ገልፀዋል::
ባለፉት አራት አመታት በሲዳማ ክልል የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብትና ደህንነት እንዳይነካ የፀጥታ ኃይሉ በትኩረት ሠርቷል ብለዋል አቶ አለማየሁ::
የፀጥታ ችግር ሊፈጠር ይችላል በሚል በወቅቱ የነበረው ስጋት እውን እንዳይሆን የሲዳማ ፀጥታ ኃይል ላበረከተው አዎንታዊ አስተዋጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል::
የክልሉ ሠራዊት በኢትዮጵያዊነት ታንፆ የተደራጀ ነው ያሉ ሲሆን የክልሉ የተረጋጋ ሠላም የሚመነጨውም ከዚሁ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ነው ብለዋል::
ሽኝት የተደረገላቸው የፖሊስ ሠራዊት አባላትም ኢትዮጵያን የመጠበቅ ኃላፊነት የተጣለባቸው መሆኑን ተገንዝበው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል::
“በምንኖርበት ምድር ሁሉ ለሰው ልጅ ደህንነት ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል” ሲሉም አሳስበዋል::
የቀድሞ የደቡብ ክልል ፖሊስ ሠራዊት ለሲዳማ ክልል ፖሊስ ሠራዊት ልምድና ድጋፍ በመስጠቱም ምስጋና አቅርበዋል::
የአንዳችን እጣ ፈንታ ከሌላው ጋር የተሳሰረ ነው ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዱፀ ታምሩ ናቸው::
የአንዱ ክልል ሠላም ሙሉ ሊሆን የሚችለው የሌሎች ክልሎች ሠላም ሲጠበቅ በመሆኑ በቀጣይም ሠላማችንን በጋራ በመጠበቅ የህዝባችንን ደህንነት ዘላቂ ማድረግ ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል::
የአራቱም ክልሎች አደረጃጀት አስተማሪና ዘመናዊ በሆነ መንገድ ተጠናቆ ለዛሬው ቀን በመብቃታችንም እንኳን ደስ አለ ብለዋል ኮሚሽነር ዱፀ::
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ በበኩላቸው የሲዳማ ክልል የቀድሞ የደቡብ ክልል ፖሊስ አባላትን አቅፎ እና ተንከባክቦ በማቆየቱ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል::
የሲዳማ ህዝብ ቅን፣ አቃፊ እና ከራሱ አስበልጦ ለሌላው ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑንም ገልፀዋል::
የቀድሞ ደቡብ ክልል ፖሊስ አባላት በክልሉ የነበሩ 56 ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ሠላምና ደህንነት ያስጠበቀ ነው ሲሉ ተናግረዋል::
ኃላፊዎቹ የሠራዊት አባላቱን የመሸኘት ሂደት በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ በሳል የመሪነት ሚናን ለተወጡ ለየክልሎቹ ርዕሳነ መስተዳድሮች እና የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ምስጋና አቅርበዋል::
በመርሀግብሩ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ የጋራ ንብረቶችን የሲዳማ ክልል የፀጥታ ሀይል ጥበቃ እንዲያደርግ የሚያስችል የመተማመኛ ሰነድ ላይ ስምምነት ተፈራርመዋል::
የመተማመኛ ሰነዱ ክልሎቹ አንድ ላይ በነበሩ ጊዜ ያፈሯቸውን የጋራ ሀብቶችን በምን አይነት መልኩ መጠበቅ እንዳለበት የሚያትት መሆኑን የፕሮጀክት ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ፀሀፊ አቶ ኑሪዬ ሱሌ ገልፀዋል::
በመሆኑም በሀዋሳ ከተማ የሚገኙትን የክልሎቹን የጋራ ሀብት የሲዳማ ክልል የፀጥታ ሀይል እንዲጠብቅ ኃላፊዎቹ በሰነዱ ላይ ተፈራርመዋል::
የመተማመኛ ሰነዱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዱፀ ታምሩ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ ለሲዳማ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ አስረክበዋል::
የክልሉ የፖሊስ ሠራዊትም የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል::
የሲዳማ ክልል መርሀግብሩ የተሳካ እንዲሆን አስተዋፅፆ ላበረከቱ ለደቡብ ኢትዮጵያ እና ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች እውቅናና ሰርቲፊኬት ያበረከተ ሲሆን በሲዳማ አባቶችም ምርቃት ተከናውኗል::
ዘጋቢ፡ ማሬ ቃጦ
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ