የአርብቶ አደር ማህብረሰብ ክፍሎችን ሁሉ አቀፍ ለውጥ ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ታረቀኝ ሀብቴ

ሀዋሳ፡ ጥር 12/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአርብቶ አደር ማህብረሰብ ክፍሎችን ሁሉ አቀፍ ለውጥ ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ታረቀኝ ሀብቴ ገለፁ።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ እንደገለፁት መንግሥት የአርብቶ አደር ማህብረሰብን ኑሮ ለማሻሻል ልዩ ፖሊሲ ቀርፆ እየሠራ ይገኛል።

ለአርብቶ አደሩ ለውጥ የማይሆኑ ኋላ ቀር እና ጎታች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማስቀረት በቀጠናው የተሻለ ሠላም እንዲሰፍን እና ለውጥ እንዲመዘገብ ከ58 ሺህ በላይ ለሆኑ አርብቶ አደሮች ግንዛቤ መፈጠሩን አቶ ማዕከል ገልፀዋል።

የአርብቶ አደር አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት ያለውና በዚህ ልክ የውሃ አማራጮች መኖሩን አቶ ማዕከል ጠቅሰው ይህንን ፀጋ ወደ ተግባር በመቀየር ለተሻለ ለውጥ እየተሠራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ታረቀኝ ሀብቴ እንዳሉት በአርብቶ አደር አካባቢ ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥ በክልሉ እየተሠራ ይገኛል።

ይህ እንዲሳካ በየደረጃው የሚገኙ አካላት በሙሉ የድርሻቸውን እንዲወጡ የቢሮ ሀላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

በቱሪዝም ሀብትና በእምቅ የተፈጥሮ ማዕድናት የበለፀገው አርብቶ አደር አካባቢ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለውጥ እንዲያስመዘግብ ቢሮው ከልማት አጋር አካላትና በአካባቢው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ከተሠማሩ እና ከሌሎች ጋር በቅንጅት እየሠራ ስለመሆኑም አስረድተዋል አቶ ታረቀኝ።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን