በሀገሪቱ በጤና መድህን አገልግሎት 54 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል – የጤና ሚኒስቴር

በሀገሪቱ በጤና መድህን አገልግሎት 54 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል – የጤና ሚኒስቴር

ሀዋሳ፡ ጥር 10/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀገሪቱ በጤና መድህን አገልግሎት 54 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ምርታማና ጤናማ ዜጋ በማፍራት ሁለንተናዊ ብልጽግናን በክልሉ ማረጋገጥ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ አሳሰቡ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ከጤና መድህን አገልገሎት አርባምንጭ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ጋር በመቀናጀት የ2016 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ንቅናቄ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

የደቡብ አትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የንቅናቄ በድረክ ላይ እንደተናገሩት በክልሉ በጤናው ዘርፍ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የጤና ቀውስ ናቸው።

እነዚህን የማህበረሰብ ቀውሶችንና ስብራቶችን ለመጠገንና ወሳኝ ውጤት ለማምጣት እንደ ክልል ከፍተኛ ርብርብ እያደረግን እንገኛለን፤ በዚህም ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ ብለዋል።

የዚሁ አካል የሆነው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት የተሳካ እንዲሆን የላቀ ጥረት ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል።

ጤናን በአግባቡ በመምራትና ችግሮችን በመፍታት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል አቶ ጥላሁን ከበደ።

ምርታማና ጤናማ ዜጋ በማፍራት ሁለንተናዊ ብልጽግናን በክልሉ ማረጋገጥ ይኖርብናልም ሲሉ ተናግረዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

የኢፌዲሪ ጤና ምኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ድጉማ፤ እንደሀገር በጤና መድህን አገልግሎት 54 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንና ከእነዚህም 12 ሚሊዮን በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ በዚህ ልክ ለማሳካት አመራሩ ቁርጠኛ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥ ውስንነት፣ የአንዳንድ ጤና ባለሙያዎች የስነ-ምግባር ችግርና የመድሀኒት እጥረት የጤና መድህን አገልግሎቱ ላይ ተግዳሮት የፈጠረ ቢሆንም የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም የመንግስት ሰራተኞች የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ከቀይ መስቀል ጋር የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንደሻው ሽብሩ በበኩላቸው እንዳሉት በጤናው ዘርፍ ተቀርጸው ተግባራዊ በመደረግ ላይ ካሉ አጀንዳዎች አንዱ የጤና መድህን ስርአት ነው።

እንደ ሀገር የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ስርአት ትግበራ አበረታች ውጤት እየተመዘገበበት እንደሆነና ክልላችንም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ከተመዘገበባቸው ክልሎች ውስጥ ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም በጤና መድህን አገልግሎት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ሰፊ ስራ እየሰሩ መሆኑንና በአጭር ጊዜ ውስጥ አዳዲስ አባላትን ማፍራትና ነባሮችን የማደስ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

በመርሀ ግብሩ በጤና መድህን አገልግሎት ዘርፍ የገቢ አቅም የሌላቸውን የደገፉ ግለሰቦችና በዘርፉ የላቀ አፈጻጸም ያመጡ ተቋማት የሰርተፍኬትና የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል።

ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን