ሚዲያው በማህበረሰቡ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ህይወት ላይ እየፈጠረ ያለውን በጎ ተጽዕኖ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለፀ

ሚዲያው በማህበረሰቡ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ህይወት ላይ እየፈጠረ ያለውን በጎ ተጽዕኖ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ጥር 10/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሚዲያው በማህበረሰቡ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ህይወት ላይ እየፈጠረ ያለውን በጎ ተጽዕኖ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገልጿል፡፡

በደቡብ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ሚዛን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የ2016 በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት አፈፃፀም ገምግሟል፡፡

በዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ላይ የተቋሙ አስተዳደር አካላት ጋዜጠኞችና ሌሎች የተቋሙ ሠራተኞችም የተሳተፉ ሲሆን ሪፖርቱን ያቀረቡት የተቋሙ የዕቅድ ዝግጅት ለውጥ ክትትል ግብረ መልስ ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መካሻ ከበደ ናቸው፡፡

በግማሽ ዓመት በተቋሙ ይዘት ዘርፍ የተከናወነው የሬድዮና የቴሌቪዥን ዜናና ኘሮግራም ዝግጅትና ስርጭት ከባለፉት 3 ዓመታት ጋር በንጽጽር የቀረበ ሲሆን በአፈፃፀሙ የተሻለውን ጎን በማስቀጠል ዝቅ ያለውን ለማሻሻል መረባረብ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

ከማስታወቂያና ገበያ ልማት ስራ ዘርፍ በግማሽ ዓመት ከ917 ሺህ ብር በላይ ዕዳ ለመሰብሰብ ታቅዶ 1 ሚሊዬን 75 ሺህ 109 ብር መሰብሰብ መቻሉም በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡

በቀረበው ሪፖርት መሠረትም ሚዲያው በአድማጩ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ህይወት ላይ ባስገኘው በጎ ተጽዕኖ ሚዲያው ስራ ላይ ባጋጠሙ ተግደሮቶች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

ተስታፊ ጋዜጠኞችም ተቋሙ ስምሪት በሚሰጣቸው ጊዜ የሚከፈላቸው ውሎ አበል የወቅቱን ገበያ ያላገናዘበ በመሆኑ ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረጉ ስለሆነ እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡

አሁን አገልግሎት እየሰጠ ያለው የቴክኖሎጂ ዕቃ ዘመናዊ ባለመሆኑና ያረጀ በመሆኑ የተዘጋጁትን መረጃዎች እያበላሸ ስለሚገኝ ተቋሙ ይህንን እንዲያስተካክል ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ከሠራተኛ ደረጃ እድገትና ጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ ክልሉ ለተቋሙ የሰጠው የሰው ኃይል መዋቅር ሰራተኛው ካለበት መደብ ወደ ሌላ መደብ የማያሳድግ እንደዚሁም በሰራተኛው መካከል ፉክክር የማይፈጥር ስለሆነ መጠናት እንዳለበትም ገልፀዋል፡፡

ሚዲያው የመንግስት እንደመሆኑም የክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ምልከታ በማድረግ ተቋሙ የተሻለ ስራ መስራት እንዲችል ክትትል እንዲያደርግ ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

የተቋሙ የይዘት ዘርፍ አስተባባሪና ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ መኮንን ኢያርዝ በበኩላቸው ጋዜጠኞች አድማጭ ተኮርና የአድማጭ ተሳትፎን የሚጨምር ዘገባ በመስራት ሚዲያውን ተደማጭ ለማድረግ ተግተው እንዲሰሩ አስገንዝበዋል፡፡

የተቋሙ ስራ አስኪያጅ አቶ ትዕዛዙ ኬንጫ የተቋሙ ጋዜጠኞችና ሰራተኞች በተቋሙ የነበረውን የበጀት እጥረት በመቋቋም ባለው ውስን በጀት ላከናወኑት ተግባርና ለተመዘገበው ጥሩ ውጤት አመስግነዋል።

የበጀት እጥረት ላለፉት 3 ዓመታት በተቋሙ ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን አውስተው ይህ ሊሆን የቻለው በፋይናንስ በጀት ቀመር መሠረት በየዓመቱ 10 ፐርሰንት እያደገ መበጀት ሲገባ ያንን ያልተከተለ ለ3 ዓመታት ተመሳሳይ የስራ ማስኬጃ ክልሉ ስለመደበ አጠቃላይ የተቋሙን ስራ በሚፈለገው ልክ ማከናወን አለመቻላቸውን አብሪርተዋል፡፡

በቀጣይም ይህ ችግር ካልተፈታ በተቋሙ ስራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚያስከትል ለክልል መንግስት በማሳወቅ ምላሹን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

የተደራሽነት ችግር ለመፍታት ተብሎ ከዚህ ቀደም በቤንች ሸኮ ዞን ሼይ ቤንች ወረዳ አካባቢ ተተክሎ የነበረውና አገልግሎት ሳይሰጥ የቆመውን ማቀባበያ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

አጠቃላይ በተቋሙ የሚስተዋለውን የአፈፃፀምና ሌሎች እጥረቶችን ለመቅረፍ ሠራተኞች የጥራት ቡድን ውይይት ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ችግሮችን እየፈቱ መስራት እንደሚገባቸው አቶ ትዕዛዙ አስረድተዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ወሰኑ ወዳጆ – ከሚዛን ጣቢያችን