የዜማ መሳሪያዎችና አልባሳትን ጨምሮ የተለያዩ ንዋያተ ቅዱሳት በቤተ ክርስቲያን ስርዓት የሚከበሩ በዓላት ድምቀት መሆናቸው ተገለፀ

የዜማ መሳሪያዎችና አልባሳትን ጨምሮ የተለያዩ ንዋያተ ቅዱሳት በቤተ ክርስቲያን ስርዓት የሚከበሩ በዓላት ድምቀት መሆናቸው ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ጥር 10/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዜማ መሳሪያዎችና አልባሳትን ጨምሮ የተለያዩ ንዋያተ ቅዱሳት በቤተ ክርስቲያን ስርዓት የሚከበሩ በዓላት ድምቀት ናቸው ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ንጉሤ ባወቀ ተናግረዋል።

ንዋያተ ቅዱሳቱ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አልፎ  የሀገር ቅርስ እንደመሆናቸው የተለየ ጥበቃና እንክብካቤ ልደረግላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ንጉሴ ባወቀ እንደገለፁት፤ ቤተክርስቲያኒቱ ዘመን ተሻጋሪ  ቅርስ የሆኑ የተለያዩ የዜማ መሳሪያዎችና ንዋያተ ቅዱሳት ባለቤት ናት።

ንዋያተ ቅዱሳቱ በዚህ የጥምቀት በዓልም ሆነ በማናቸውም የቤተክርስቲያኒቱ በዓላት  የተለያዩ ህብረ ቀለማትን በተላበሱ የሰንበት ትምህርት ቤት ዝማሬዎችና ያሬዳዊ ዜማዎች  የተለየ  ግርማ ሞገስ የሚያላብሱ  ስለመሆናቸው ዋና  ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል። 

ስለሆነም በገናን፣ ከበሮን፣ መቆሚያን፣ ዋሽንትን፣ ጽናጽልንና የተለያዩ አልባሳትን ጨምሮ ያሉ  ሌሎችም  ንዋያተ ቅዱሳት  ከቤተ ክርስቲያኒቱ አልፎ  የሀገር ቅርስ እንደመሆናቸው የተለየ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሀገረ ስብከቱ ዋና ፀሐፊ መጋቢ ጥበብ ወርቁ ተክሌና ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ሊቀ ስዩማን ቀሲስ አፈወርቅ ኃይሌ በበኩላቸው  የቤተክርስቲያን ሊቃውንትና ሰንበት ትምህርት ቤት በማናቸውም መንፈሳዊ አገልግሎቶች  ወቅት ከንዋያተ ቅዱሳትና የቤተ ክርስቲያኒቱ የዜማ መሳሪያዎች ጋር  የላቀ ቁርኝት ያላቸው ስለመሆኑ ገልፀዋል።

በዚህ የአደባባይ በዓል በሆነው  የጥምቀት በዓል ሰንበት ትምህርት ቤቱና የቤተ ክርስቲያኒቱ  ሊቃውንት ያሬዳዊ ዜማ እንዲሁም  ደማቅ ህብረ ቀለም የተላበሱ ዝማሬዎችና ሌሎችም መንፈሳዊ አገልግሎቶች በዓሉ  የተለየ እይታ በማግኘት በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት  በዩኔስኮ እንዲመዘገብ  አበርክቷቸው ጉሊህ እንደሆነም በመጠቆም።

የሃይማኖት አባቶቹ የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ በሠላማዊ ሁኔታ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።

ዘጋቢ:  አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን