የጥምቀት በዓል ኃይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ፣ አብሮነትና አንድነትን በሚያደምቅ መልኩ ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል’’ –  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ንጉሴ ባወቀ

የጥምቀት በዓል ኃይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ፣ አብሮነትና አንድነትን በሚያደምቅ መልኩ ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል’’ –  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ንጉሴ ባወቀ

ሀዋሳ፡ ጥር 09/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጥምቀት በዓል ኃይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ፣ አብሮነትና አንድነትን በሚያደምቅ መልኩ ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል’’ ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ንጉሴ ባወቀ ተናገሩ።

በዓለ ጥምቀቱ  በሆሳዕና ከተማ  ሃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር በቂ ዝግጅት መደረጉም ተገልጿል።

መልአከ ሕይወት ቀሲስ ንጉሴ ባወቀ በዓሉን አስመልክተው እንደገለጹት በዓሉ ኃይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀና በደመቀ መልኩ እንዲከበር በሀገረ ስብከቱ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በተለይም በሆሳዕና ከተማ ከየአቅጣጫው ታቦታት ወደ ጥምቀተ ባህሩ የሚወርዱባቸውን መንገዶች፣ የታቦታት ማረፊያ ቦታዎችን የማጽዳት፣ ከተማዋን የማስዋብ ስራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ መሆናቸውን  ዋና ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

ጥምቀት በክልሉ ማዕከል የሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦች በአንድነት አምረውና ደምቀው የሚታዩበት በዓል እንደሆነም ጠቁመዋል።

የከተራና የጥምቀት በዓል እሴቱን ጠብቆ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የጠቆሙት ዋና ስራ አስኪያጁ በተላይም የከተማ ወጣቶች ምዕመኑን በማስተባበር  እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል::

ምዕመኑ ኃይማኖታዊ አስተምህሮው በሚያዘው መሰረት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ እርስ በእርስ በመፈቃቀር፣ በመከባበርና በአንድነት በዓሉን እንዲያከብሩት መልአከ ሕይወት ቀሲስ ንጉሴ ባወቀ ጥሪ አቅርበዋል::

ከዚህ በተጨማሪም ህዝበ ክርስቲያኑ የጥምቀት በዓል ሲያከብር እርስ በእርስ በመደጋገፍ፣ ያለው ለሌለው በማካፈል፣ የታረዙትን በማልበስና የተጠሙትን በማጠጣት ሊሆን እንደሚገባም አመላክተዋል።

የጥምቀት በዓልን በዝማሬ፣ በምስጋናና በእርጋታ በማክበር ታቦታቱ ካደሩበት ባህረ ጥምቀት ወደ መንበራቸው በሰላም እንዲገቡም ተገቢውን እገዛ ማድረግ እንደሚገባም መልክዕት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ: በየነ ሰላሙ – ከሆሳዕና  ጣቢያችን