በካፋ ዞን የወሽ፣ ጎፓ-ደቂያ የ18 ኪሎ ሜትር መንገድ ፕሮጀክት ተጠናቅቆ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ተጠየቀ
ለዘመናት የህዝብ ጥያቄ ሆኖ የቆየዉ በካፋ ዞን የወሽ፣ ጎፓ-ደቂያ የ18 ኪሎ ሜትር መንገድ ፕሮጀክት ተጠናቅቆ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል ባለድርሻ አካላት የጋራ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
ለመንገዱ ግንባታ 12 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን በእስካሁኑ የተገኘው 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ በመሆኑ ሥራውን ለማጠናቀቅ የሚያስችል የባለድርሻ አካላት የጋራ ምክክር መድረክ በዴቻ ወረዳ ደቂያ ቀበሌ ተካሂዷል።
በዉይይቱ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዋና ኦዲት ቢሮ ኃላፊ አቶ አስራት አበበ እንደገለጹት አካባቢው ለዘመናት የመንገድ መሠረተ ልማት ተደራሽ ችግር ስለነበረበት ህብረተሰቡ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲዳረግ ቆይቷል ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አካባቢው ዕምቅ የቱሪዝምና የተፈጥሮ ሀብት ፀጋ ባለቤት ቢሆንም በመንገድ መሠረተ ልማት እጥረት መጠቀም ያለመቻሉን አቶ አስራት ተናግረዋል።
የክልሉ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን የቦንጋ ዲስትሪክት፣ አዳዲስ 21ና 17 የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ የጥገና ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የተናገሩት የቦንጋ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸዉ ጊጂ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች 5ቱን በተያዘው በጀት ዓመት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ብለዋል።
በተለይ የወሺ-ጎፓ-ደቂያ መንገድ መገንባት ዴቻንና ሺሾ እንዴ ወረዳ ቀበሌዎችን ለማገናኘት እንዲቻል የተጀመረውን የ18 ኪሎ ሜትር መንገድ ከማከናወን አንጻር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያለዉን ማሽን በመጠቀምና ህብረተሰቡን በማስተባበር አሁን ላይ የአፈር ስራን ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቅ መቻሉን አቶ ግዛቸዉ ተናግረዋል።
አቶ ግዛቸው አያይዘውም 6 የድልድይ ስራዎች መጀመራቸውንና ለመንገድ ስራ የሚሆኑ የኮረት ማምረትና መሰል ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸው ፕሮጀክቱን በአንድ ወር ዉስጥ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየተሰራ ነዉ ብለዋል።
በህብረተሰብ ተሳትፎና በመንግስት የተሰሩ ስራዎችን ሪፖርት ያቀረቡት የመንገድ ልማት ኮሚቴዉ ሰብሳቢ አቶ በዛብህ ቡሾ የመንዱን ስራ ለማከናወን 12 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በእስካሁኑ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል ብለዋል።
በተሰበሰበው ገንዘብም የመንገድ ከፈታ፣ ቱቦ መቅበርና የጎን ግንብ ስራ፣ ለድልድይ የሚሆን ድንጋይ ማቅረብና መሰል ስራዎች መከናወናቸውን አቶ በዛብህ አክለዋል።
የመንገዱ መጀመር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለዉ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ መንገዱ ተጠናቅቆ የታሰበውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል የዞኑ አስተዳደር የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ከመንገድ መሰረተ ልማት እጦት አኳያ ለበርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ላይ መሆናቸውን የገለጹት ከዉይይቱ ተሳተፊዎች መካከል ዶ/ር አድማሱ አበበ፣ አቶ አሸብር አለሙና ሌሎችም መንገዱ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።
በዉይይቱ የደቡብ ምዕራብ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አብዲዩ መኮንን፣ የዴቻና የሺሾ-እንዴ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪዎችና ሌሎች ከፍተኛ የዞንና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል።
ዘጋቢ፡ አሰግድ ሳህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ