ከ2 ሚሊዮን በላይ ዝሪያቸው የተሻሻሉና ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆኑ የቡና ችግኞችን ለተከላ ማዘጋጀቱን ተናግሯል
ሀዋሳ፡ ጥር 06/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የይርጋጨፌ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ከ2 ሚሊዮን በላይ ዝሪያቸው የተሻሻሉና ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆኑ የቡና ችግኞችን ለተከላ ማዘጋጀቱን ተናግሯል።
አርሶአደሩ የአፈር ለምነትን በማሻሻልና ያረጁ ቡናዎችን በማደስ ምርትና ምርታማነትን ከፍ የሚያደርጉ ተግባራት ላይ አጠናክሮ መሥራት አለበት ተባለ፡፡
ከ75 ሺህ ሄክታር በላይ የቡና ሽፋን ባለው የጌዴኦ ዞን ከ3 እስከ 5 ዓመት በየዓመቱ ያረጁና ምርት የማይሰጡ ቡናዎችን በኩታገጠም በማደራጀት የማደስ ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ ከዞኑ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
በኩታ ገጠም በማደራጀት የቡና ማደስ ተግባር በንቅናቄ እየተሠራ እንዳለ የገለጹት የጌዴኦ ዞን ቡናና ቅመማ ቅመም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ተፈራ ያረጀ ቡና ሲነቀል ዘመናዊ ቡና ለመትከል የአፈር ለምነት የማሻሻል ሥራ አብሮ እየተሠራ እንዳለ ጠቁመዋል።
ቡና ሲታደስ የተሻሻለ ምርታማ ብዙ ምርት የሚሰጥ የትኛው ነው በሚል የዘር ዝግጅት ይደረጋል ያሉት የይርጋጨፌ ወረዳ ቡናና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበራ አሰፋ ለ2016 የቡና ተከላ ወቅት የሚሆን ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ከአርሶአደሩ ተጠቃሚነት ረገድ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር በሚደረገው ሂደት አርሶአደሩ ቡናን ወደ ውጪ ለመላክ አብዛኛው አርሶአደር ፍቃድ ቢወስድም ከተወሰኑት በስተቀር ወደ ውጭ መላክ አልቻሉም ያሉት አቶ አበራ ይሄም ሰፊ የቤት ሥራ እንደሚያስፈልገው ገለጸዋል።
በኋላቀር አስተሳሰብ የተተከለ ቡና አይነካም በሚል ያረጀና ምርት የማይሰጥ ቡና ይዘው ከመቀመጥ በዘመናዊ መልኩ ሠርተው መጠቀም እንዲችሉ የግንዛቤ ሥራ በስፋት መሥራታቸውን የተናገሩት በይርጋጨፌ ወረዳ ሰዴ ቀበሌ ግብርና ጽ/ቤት የግብርና ባለሙያ ንዋይ ገረመው አርሶአደሩ በዚህ ልክ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
የቡና ማደስ ተግባሩ ያለውን ፋይዳ በመረዳት ከአምና ጀምሮ ወደ ተግባር የገቡት አርሶአደሮቹ ዘንድሮም የተሻለ ለመሥራት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ውብሸት ኃ/ማሪያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ