ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ሚኒስትሮች በ

ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ሚኒስትሮች በጎፋ ዞን ከመሎ ኮዛ እና ላሃ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ

ሀዋሳ፡ ጥር 06/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በጎፋ ዞን ከመሎ ኮዛ እና ላሃ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

የላሃ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አንድነት ጸጋዬ እና የመሎ ኮዛ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ምናሴ ኤሊያስ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ በአከባቢው በከፍተኛ ሁኔታ የሚመረተውን የሰሊጥ፣ ማሾ፣ ቡና፣ ኮረሪማ፣ ሙዝ እንዲሁም ሌሎች የግብርና ምርቶችን ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማድረስ የሚያስችል የመንገድ ችግር ፈተና እንደሆነባቸው አንስተዋል።

በጤና ተቋማት፣ በመብራት፣ በውሃ እና በመሳሰሉት መሰረተ ልማቶች የሚታዩ ችግሮች እንዲፈታም ጥያቄ አቅርበዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ፋንታዬ በበኩላቸው፥ አንድ ሆነን ተባብረን ከሰራን ብልጽግና ፓርቲ የማይፈታው ችግር የለም ሲሉ ነው ያስረዱት።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፥ የተነሱ ጥያቄዎችና አስተያዬቶች ተገቢ መሆናቸውን አንስተው መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ በበኩላቸው በወረዳው ያሉ የግብርናና የተፈጥሮ ሀብቶች ለአካባቢው መበልፀግ ምቹ ዕድልን የሚፈጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአከባቢው ጸጋ በአግባቡ በማልማት የብልጽግና ተስፋ ለማድረግ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

አከባቢው ኮይሻ ፕሮጀክት አቅራቢያ የሚገኝ በመሆኑ ቀጠናውን የልማት ኮሪደር ለማድረግና የኢትዮጵያን የጋራ ብልጽግና ለማረጋገጥ መንገድ ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ መፍትሔው ላይ ትኩረት እንሰጣለን ብለዋል።

ሚኒስትሮቹ በመሎ ኮዛ ወረዳ የሚመረቱ የግብርና ምርት ሂደቶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን