ኮሌጁ ሙያዊ ስነምግባሩን ያከበረ በእውቀት ታንጾ ህብረተሰቡን በተገቢው የሚያገለግል ባለሙያ ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

ኮሌጁ ሙያዊ ስነምግባሩን ያከበረ በእውቀት ታንጾ ህብረተሰቡን በተገቢው የሚያገለግል ባለሙያ ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ጥር 02/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሙያዊ ስነምግባሩን ያከበረ በእውቀት ታንጾ ህብረተሰቡን በተገቢው የሚያገለግል ባለሙያ ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የሚዛን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አስታወቀ።

ኮሌጁ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የሚሰለጥኑ 683 አዳዲስ ተማሪዎችንም ተቀብሏል።

በቀድሞ የደቡብ ክልል ከአርብቶ አደሩ አካባቢዎች የተውጣጡ የአርብቶአደሩን ተማሪዎች ተቀብሎ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ማሰልጠን የጀመረው የሚዛን አማን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዛሬ ከደረጃ አራት አልፎ በመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም ተማሪዎችን በመቀበል በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በማሰልጠን ላይ ይገኛል።

ኮሌጁ በተለይም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙ ስኬታማ እንዲሆንም በወቅቱ የራሱን ድርሻ ማበርከቱንም ነው የኮሌጁ ዲን አቶ ጸጋዬ አትርሴ የተናገሩት።

ኮሌጁ አሁንም አዲስ በተዋቀረው የደቡብ ምእራብ ክልል ስር ብቸኛ ኮሌጅ ሆኖ ከክልሉ ካሉ ዞኖች የተመለመሉ በተለያየ ሙያ ሰልጥነው ሲያገለግሉ የነበሩ ባለሙያዎችን በሙያ ማሻሻል ፕሮግራም 164 ተማሪዎችን ተቀብሎ ስልጠናዎችን በመጀመሪያ ዲግሪ እየሰጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ከዚህ ባለፈ በሀገር አቀፍ ፈተና ወስደው የመግቢያ ውጤት ያልመጣላቸው እና በቲ ቪቲ እንዲታቀፉ የተደረጉ 683 አዳዲስ መደበኛ ተማሪዎችን ከየዞኖቹ ተቀብሎ የመግቢያ የምዘና ፈተና በመስጠት ያለፉትን ተማሪዎች በ7 የትምህርት ዘርፎች ተቀብሎ በመጀመሪያ ዲግሪ በማሰልጠን ላይ መሆኑን ነው የኮሌጁ ዲን አቶ ጸጋዬ የተናገሩት።

የመማር ማስተማሩን ተግባር ጥራት ባለው መንገድ ለማስቀጠል፣ መምህራንን በስልጠና የማብቃት እና ተማሪውም ጊዜውን በተገቢው በትምህርት ላይ እንዲያሳልፍ ከመደበኛው ስልጠና ባለፈ የቤተ ሙከራ እና ቤተመጽሀፍቶች በማደራጀት ተገቢውን እውቀት እንዲገበይ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በግቢው ያለውን የተማሪ ክፍል ጥበትም ለመቅረፍ እንዲሁም የግቢ በር ግንባታ ኮሌጁ 40 ሚሊየን በሚጠጋ ወጪ ተጨማሪ ግንባታዎችንም እያከናወነ መሆኑን ነው ዲኑ የተናገሩት።

ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን