ኢትዮጵያ የገጠሟትን በርካታ ተግዳሮቶች በማለፍ ከአፍሪካም አልፋ ለአለም ምሳሌ የሚሆን ኢኮኖሚያዊ እመርታ አሳይታለች – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ
ሀዋሳ፡ ጥር 02/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ኢትዮጵያ የገጠሟትን በርካታ ተግዳሮቶች በማለፍ ከአፍሪካም አልፋ ለአለም ምሳሌ የሚሆን ኢኮኖሚያዊ እመርታ ማሳየቷን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለፁ::
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አዘጋጅነት በኢንዱስትሪ ፖሊሲና ተኪ ምርት ስትራቴጂ ላይ በአርባ ምንጭ ከተማ ምክክር እየተካሄደ ነው።
በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመሻገር ከአፍሪካም አልፎ ለአለም ምሳሌ መሆን የሚችል ኢኮኖሚያዊ እምርታ አስመዝግባለች ብለዋል።
ለተገኘው አወንታዊ ውጤት የኢኮኖሚ ሪፎርም መደረጉ፣ የህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎና ተያያዥ ምክንያቶች እንደሆኑ አመላክተዋል።
የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከተስፋ ወደሚጨበጥ ምዕራፍ መሸጋገሩንም ጠቅሰዋል።
የሀገር ኢኮኖሚ ዘላቂና ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችል የኢኮኖሚው መሰረቱ ሀገር ባላት ፀጋ ላይ መመስረት እንዳለበት ያነሱት አቶ ጥላሁን የውጭ ድጋፍ ላይ የተመሰረተ ምጣኔ ሀብት ብዙም አያራምድም ነው ያሉት።
ለዘርፉ ውጤታማነት ጠንካራ ፖሊሲ እንደሚያስፈልግና የተዘጋጁ ፖሊሲዎችን በሚገባ መረዳትና ወደተግባር መቀየር ይገባል በማለት አሳስበዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ የተዘጋጁ የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎችን በሚገባ በመረዳት ለውጥ ለማምጣት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው ኢትዮጵያ እራሷን በኢንዱስትሪ ለማሳደግ በርካታ ፀጋዎችን የተጎናፀፈች ሀገር ስለመሆኗ አንስተው በቂ የሰው ሀይል፣ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት፣ ተመራጭ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ በቂ የሀይል አማራጮችና የማዕድን ሀብት የኢትዮጵያ ልዩ መገለጫዎች ናችው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም ለዕድገት ጥሩ ዕድል ፈጣሪ መሆኑን ሚኒስትሩ አንስተዋል።
ጠንካራ ኢኮኖሚ የጠንካራ ፖሊሲ ውጤት ነው ያሉት አቶ መላኩ ፖሊሲውን ወደውጤት ለመቀየር ደግሞ ግንዛቤ ያለው ጠንካራ አመራር ይፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ሀገሪቱ ያላትን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ መልሶ መቃኘት እንዳስፈለገና በአዲስ መልኩ እየተዘጋጁ ባሉ ፖሊሲዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ ነው መሆኑን አንስተዋል።
አዲስ እየተዘጋጀ ያለው ፖሊሲ ለተኪ ምርቶች ትኩረት መስጠት፣ የግል ባለሀብቶች በዘርፉ በሰፊው እንዲሳተፉ ማድረግ፣ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ልዩ ትኩረት መስጠትና የኢንዱስትሪ ክላስተር መፍጠር የፖሊሲው ዋና ዋና ትኩረቶች ናቸው ብለዋል አቶ መላኩ አለበል።
ምርትን ማሳደግ፣ የአምራቾችን ቁጥር ማብዛት፣ የስራ ዕድል መፍጠርና የኢትዮጵያ ብልፅግናን ማረጋገጥ የፖሊሲው መዳረሻዎች መሆናቸው ተመላክቷል።
በዚህ የጋራ መድረክ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፀሀይ ወራሳ፣ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባውዲ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ፣ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች፣ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች፣ የስራ ሀላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡
ዘጋቢ፡ ጀማል የሱፍ
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ